The Tale of The Skeptic
[Not Based on a True Story 😅]
ጊዜ የእግዜር ጅራፍ ፥ የዲያብሎስ በትር
እኛን ጥሎ ሊሄድ ፥ ሁሌም የሚታትር
ገና አበብን ስንል ፥ ያዪናል ተቀጥፈን
በጊዜ አለንጋ ነው ፥ እግዜር የሚገርፈን!
፨
ጉዱን ያላወቀ ፥ የሀገር ሰው ደጉ
"መረቅኋችሁ" ብሎ ፥ ይለናል "እደጉ!"
የልጅ ሳቃችንን ፥ ገፊ ዕድሜ ከቀማን
ማደግ አይደለም ወይ ፥ ትልቁ እርግማን?
፨
እንዳሉት አደግን ፥ እንደ ምርቃቱ
አንዲህ ቅርብ ነው ወይ ፥ መጎልመስ ርቀቱ?
ገና ትላንትና ፥ አልነበርን ወይ ልጆች?
ከመቼው ዳበሱን ፥ የዕድሜ ሸካራ እጆች?
፨
ሰኞ ነው ማክሰኞ ፥ ዕሮብ ነው ወይ ሐሙስ?
ጡጧችንን ጥለን ፥ የጨበጥነው ጠርሙስ
ከእንቅልፍ ስንነቃ ፥ የሆነ ቀን ድንገት
ጨብጠን ተገኘን ፥ የብርሌ አንገት
ስኳርን በስካር ፥ ሐሴት በሴት ተካን
ኀዘን ደስታችን ፥ በመለኪያ ለካን
እየጠጣን ቢራ ፥ ካገኘንም ውስኪ
በኒቼን ተዝናናን ፥ በዶስትዮቭስኪ
እሳት ይስም ጀመር ፥ ከንፈሬ ቀንበጡ
የሲጋራ ቁሩ ፥ ጣቶቼም ጨበጡ
ጊዜ አስገድዶ ፥ ትምባሆ አስማገን
ልጆች አልነበርን ወይ ፥ ማን አባት አረገን?
፨
በየት መንገድ አልፈን ፥ እዚህ ጋር ደረስን?
ከረሜላ ንቀን ፥ የሴት ከንፈር ላስን?
ከሴት ጭን ከወጣን ፥ ሳይሞላ እንኳ መንፈቅ
ማነው ያስተማረን ፥ የሴት ጭን መናፈቅ?
ጊዜ በጉልበቱ ፥ እያሳጣን ተገን
ንጹሕ ምንጭ ነበርን ፥ ድፍርስ ወንዝ አረገን!
፨
ደጀ ሰላም ሳሚ ፥ አልነበርን ወይ ጸላይ?
መቼ ነቅተንበት ፥ ጢቅ አልን እግዜሩ ላይ?
"አምላክ እንደሁ የለም ፥ ቢኖርም አይገደን
አለማወቅ እንጂ ፥ ለእርሱ ሚያሰግደን
እግዜር ይሁን ሰይጣን
ኢምንት ዕድሜያችን ላይ ፥ የላቸውም ሥልጣን!"
እያልን ተቆጣን
ለምናየው ሁሉ ፥ ውድም ግድም አጣን!
፨
"አልነጋም" እያልን ፥ ሲለን "አኩኩሉ"
ሳንደበቅ ያዘን ፥ አይ ጊዜ ችኩሉ
መሀሉ ጋር ሳንደርስ ፥ አየነው ጥጋቱን
ይመሽብን ጀመር ፥ ሳናውቀው መንጋቱን!
፨ ፨ ፨
