እስትሮክ ለምን ሰውን ያጠቃል? መከላከል የምንችላቸው 23 እስትርክ አጋላጭ መንስኤዎች: አንጎል በቅፅበት… — Hakim — TG.ME

እስትሮክ ለምን ሰውን ያጠቃል?

መከላከል የምንችላቸው 23 እስትርክ አጋላጭ መንስኤዎች:

አንጎል በቅፅበት የደም ዝውውር ሲቋረጥበት የሚከሰት ህመም ነው እስትሮክ። እስትሮክ በሩቅ በስሚ ስሚ ይታወቅ ነበር።

አሁን ግን ስርጭቱ ተበራክቷል። ብዙ ሰዎችን በቅፅበት እንዳልሆኑ እያደረገ ያለ ከባድ የአንጎል ህመም ነውና ምን እናድርግ?

መከላከል ከየትኛውም የህክምና አማራጭ በላይ አዋጭ ነው። ውጤቱም ያማረና አስተማማኝ ነው። እስትሮክን በሚገባ በመከላከል መርህ መቆጣጠር ይቻላል።

ሐያ ሶስት የሚደርሱ አጋላጭ መንስኤዎች ከመቶው 84 እጁን እስትሮክ አምጪዎች ውስጥ ይሸፍናሉ። በሰው ልጅ አቅም ማስተካከል የሚቻሉት በጣም ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ ማለት ነው።

እስትሮክ በቁጥር ሲገለፅ ቀላል አይደለም። በየ2 ሴኮንዱ በአለም ላይ አንድ ሰው በእስትሮክ ይጠቃል። በየ4 ሴኮንዱ አንድ ሰው በእስትሮክ ለሞት ይዳረጋል። ከአራት ሰዎች አንዱ እስትሮክ ያጋጥመዋል (የሒወት ዘመን ተጋላጭነት አሐዝ ነው)።

በየአመቱ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እስትሮክ ይይዛቸዋል። ግማሽ የሚሆኑት ለህልፈት ይዳረጋሉ። ይኸ መረጃ እስትሮክ ምን ያክል አሳሳቢ እንደሆነ ይጠቁመናል። በመከላከል የምንከላከለው መሆኑ ጥሩ ቢሆንም ግንዛቤ አለመኖሩ መጥፎ ጎን ነው።

1ኛ ቁጥር አንድ የእስትሮክ መንስኤ የደም ግፊት መጨመር ችግር ነው።

የደም ግፊትን በተገቢው መንገድ መቆጣጠር ይገባል። የደም ግፊት መጨመር ምልክት የማያሳይ በመሆኑ ለመዘናጋት ዳርጎ መጨረሻ ላይ ዱብዳ ሆኖ ይመጣል። አድፍጦ ብቅ ሲል የማይታመን ነው የሚሆነው።

የደም ግፊት ህክምና የሚወስዱ ጥቂቶች ናቸው። መች ታመምኩና ነው መልሳቸው። እኛ የምንለው የደም ግፊት መጨመር ምልክት አልባ ሆኖ የሚቆይ እና መጨረሻ ላይ ከባድ ችግር የሚፈጥር ነው። ሰሚ የለም።

እስትሮክ ግማሽ ሰውነታቸውን ካሳጣቸው በሗላ ምነው ያኔ በወሰድኩ አያድንም። ቀድሞ የህክምና መርሆችን ይከተሉ።

2ኛ የስኳር ህመም ነው።

የስኳር ህመም ሌላው ምልክት የማያሳይ ስር የሰደደ ህመም አይነት ነው። ያለ ምልክት ለብዙ አመታት ይቆያል። ያ ማለት ግን ችግር አይፈጥርም ማለት አይደለም። ውስጡስጡን የደም ስሮች ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ይቆያል። መጨረሻ ላይ ለእስትሮክ አለያም ለልብ ህመም ይዳርል።

ሁለቱም ድንገተኛ ሆነው ነው የሚመጡት። ክስተቱ ድንገተኛ ሆነ እንጂ ሒደቱ ረዘም ያለ አመታትን የፈጀ ነው። ህክምና ሒደቱን በመግታት ሊፈጠር የሚችለውን መዘዝ ይታደጋል። መከላከል ያ ነው።

ከአንድ ጀምነር 23 ድረስ እስከምንደረስ በመጀመሪያ እነዚህ ሁለቱን መረዳታችንን እንወቅ። የደም ግፊትና ስኳር መርመራ ማድረጋችንን እንጠይቅ። አለባችሁ ከተባለ ምን እርምጃ ወሰድኩ ብለው ይጠይቁ?

በቀጣሪ ቀሪ 21 አጋላጭ መንስኤዎችን ተራ በተራ ወደ እናንተ እናደርሳለን። ሁለቱን ይወቁ፤ ይከላከሉ። ሌለው እነዚህን ተከላከልን ማለት እስትሮክን ብቻ አይደለም የምንከላከለው ቀሪ የሰውነት ክፍሎች ህመሞችን ጭምር ነው። አትራፊ ይሆኑበታል።

References

1) doi: 10.1177/17474930241308142. Epub 2025 Jan 3. PMID: 39635884; PMCID: PMC11786524.

ዶ/ር መስፍን በኃይሉ: የአንጎል ፣ ህብረ-ሰረሰር እና ነርቭ-ዘንግና ጡንቻ ህክምና

@HakimEthio
❤19
August 31, 2026 3.5K 18