“ቆሽቴ አረረ” ስንል?
ኢትዮጵያዊያን ሲናደዱ፣ ሲጨነቁ፣ በንዴት ድብን ሲሉ ‘ቆሽቴ አረረ’ ይላሉ። በእርግጥ ስንበሳጭ ቆሽት ላይ ምን ጉዳት እንደሚፈጠር እና ከስኳር በሽታ ጋር ምን ግንኙነት አለው?
ቆሽት በሆድ ውስጥ የሚገኝ ኤንዛይም እና ሆርሞን የሚያመነጭ የሰውነት ክፍላችን ነው። ቆሽት ኢንሱሊን የሚባል ወሳኝ ሆርሞን ያመነጫል። የኢንሱሊን ሆርሞን ዋና ተግባሩ ለሰውነታችን ተቀዳሚ ነዳጅ የሆነውን ግሉኮስ ወደህዋሶቻችን እንዲገቡ በማገዝ ለሃይል ሰጪነት / እንደነዳጅ እንዲቃጠል ያደርጋል። ስኳሩን ከደም ውስጥ አውጥቶ ወደ ሴሎች / ህዋሳት ሰርጎ በመግባት ሰውነት ለሃይል ምንጭነት እንዲጠቀምበት ያደርጋል።
የኢንሱሊን ምርት ወይም ተግባር መስተጓጎል በሚፈጠርበት ጊዜ ስኳር ጥቅም ላይ መዋል ስለማይችል ደም ውስጥ እየተከማቸና እየበዛ መሄድ ይጀምራል። ስኳር በደም ውስጥ እየተከማቸ በጊዜ ሂደት ወደ አደገኛ ደረጃ ከፍ በማለት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይዳርጋል።
ይህ የቆሽት ሆርሞን የማምረት ስራ መስተጓጎል ሰዎች ሲናደዱ ‘ቆሽቴ አረረ’ ከሚሉት ጋር የሚቀራረብ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያዊያን “ቆሽቴ አረረ” አገላለጽ ከስኳር ህመም መነሻ ምክንያትን ያንፀባርቃል።
የተራዘመ ጭንቀት እና ከፍተኛ ጫና ሲኖርብን ቆሽት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያመጣል። ጭንቀት ብቻዉን በራሱ የስኳር በሽታን ባያመጣም ከልክ ያለፈ ጭንቀት፣ ብስጭት፣ ንዴት ወዘተ ቀስ በቀስ ለቆሽት መጎዳት እንደአንድ ተጨማሪ አጋላጭ ምክንያት ይሆናል። የቆሽት ስራ መስተጓጎል ሂደት ረዥም ዓመታትን የሚፈጅ የሜታቦሊክ ጫና እንጅ በንዴት ብቻ አይደለም።
ማስታዎስ ያለብን ቆሽትን የሚያሳርረው የአእምሮ ጭንቀት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በርካታ ጫናዎች አሉ። ጤናማ አመጋገብ ከሌለን ቆሽትን ያስጨንቃል፤ በሂደት ቆሽትን ይጠብሳል። በተቃራኒው ጤናማ አመጋገብ ስንከተል ቅሽት ያገግማል፣ ይለመልማል።
በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግም ቆሽትን ይጎዳል። ስለዚህ እየተንቀሳቀስን ቆሽታችንን እናስደስት።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት በተለይም ቦርጭ ለቆሽት አደገኛ ነው። ሸንቀጥ ስንል ደግሞ ቆሽታችን ትቦርቃለች፣ ፋታ ታገኛለች።
አልኮል እና ሲጋራ ማጨስ ለቆሽት መርዝ ናቸው። አልኮል ስንጠጣ እና ሲጋራ ስናጨስ ቆሽትን ምድጃ ላይ ጥዶ እርርርርር አድርጎ እንደማቃጠል አስቡት። ጣፋጭ ነገሮችንም ማዘውተር እንደዚያው ለቆሽት ጎጂ ነው። አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጣፋጭ ምግቦችን ስናቆም ደግሞ ቆሽት እፎይ ትላለች።
ሁሉንም ጭንቀት ከህይወት ውጣውረድ ማስወገድ ባንችልም በልክ በመቆጣጠር ቆሽት “ከመቃጠሉ በፊት” ማከም እንችላለን።
የዚህን ሙሉ ጽሁፍ በዶ/ር መላኩ ብሎግ ያገኙታል https://melakutaye.com/stress-exhausts-pancreas-when-ethiopians-say-my-pancreas-got-burned-out/
ዶ/ር መላኩ ታዬ (ኢንዶክሪኖሎጂስት)
ቴሌግራም https://t.me/hakimmelaku
ፌስቡክ https://web.facebook.com/hakimmelaku
አስተያየት ለመስጠት https://maps.app.goo.gl/twmS9fq7LiG1eRnq9
Get social with Hakim on Youtube: http://www.youtube.com/@Hakim207
@HakimEthio
25August 29, 2026 4.7K 1 14


