ማለፊያ (ፉአድ ሙና) ክፍል ሁለት *** የመውደድ በትር ቢሸነቁጠው፣ ልቧ ቢደማ፣ ጩኸት አይፈይድ ጆሮ… — 𝐇𝐚𝐟𝐮 𝐢𝐬𝐥𝐚𝐦𝐢𝐜 𝐩𝐨𝐬𝐭™🕋 — TG.ME

ማለፊያ
(ፉአድ ሙና)
ክፍል ሁለት
***
የመውደድ በትር
ቢሸነቁጠው፣ ልቧ ቢደማ፣
ጩኸት አይፈይድ
ጆሮ ተደፍኗል፣ ቃሏን ላይሰማ።
***
ቀኑን ዞር ዞር እያሉ ዋሉ። የከተማውን ዳር ቅዝቃዜ... የዝናብ መጀመሪያዋን እንጦጦ ትንፋሽ እየተነፈሱ... እንደ ህፃን እየተጫወቱ... መኪና እየነዱ... ገመድ እየተንጠላጠሉ... ዋሉ። እራት ሲደርስ ከእንጦጦ ወጥተው ከሪማ ወደምትወደው ታዋቂ ሬስቶራንት አቀኑ። ቤቱ ነጭ ተገልጋይ ይበዛዋል። ያሉት ሀበሻዎችም የዲያስፖራ ወዝ አላቸው። ምቾት የሚነበብበት ፊት በየወንበሩ አለ። እየተመረጡ የሚገቡ ይመስላል። በእርግጥ ሰውን እየመረጠ የሚያስገባው ዋጋው ነው። ገንዘብ ድኩም ፊትን ገፍቷል። የአንድ ቀን የእራት ክፍያቸው የአንድ ጀማሪ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ይሆናል።

እራቱ ቀርቦ ትንሽ እንደተጫወቱ ጀማል ወደ እህቱ ዞር ብሎ ቀኑን ሲከነክነው የዋለውን ጥያቄ አውጠነጠነ። የባህሪዋ መለዋወጥ የእርጉዝ ሴት ሆኖበታል። በልቡ «አርግዛ ይሆን እንዴ?» ሲል አሰበ። መልሶ መጠርጠሩን ረገመው። ካምፓስ የገባ ሰው ላይ የሚፈጠረው አይታወቅም ሲል ሀሳቡን ደገፈ። በእርግጥ መጠርጠሩ ለራሱም አስቀይሞታል። ግን ሳይረፍድ... አባቷ ጋር ሳይደርስ መሸፈን ያለበት ገመና ካለ መሸፈን አለበት። ለእርሷ ደግሞ ከእርሱ በላይ ገመናዋን የመሸፈን ኃላፊነት ያለበት ሰው እንደሌለ ተሰማው! ትንፋሹን ሰበሰበ።
«ሲሁ... አርግዘሻል እንዴ?» አላት። ድምፁ ይንቀጠቀጣል።
አይኖቿ እንደፈጠጡ እንባ መዘርገፋችውን ተያያዙት። ከሪማ በድንጋጤ አፏን ከፍታ ቀረች።
«ሲሁዬ... በክፋት አታስቢብኝ የተፈጠረ ነገር ካለ ተነጋግረን መፍትሔ ማበጀት አለብን ብዬ ነው።»
በህይወቱ አሁን እንዳወጣው ቃል የፀፀተው ነገር ኖሮ የሚያውቅ አይመስለውም።
«እንደዚህ ነው የምትገምተኝ?» አለቃቀሰች።
ከሪማ ደርቃ ቀርታለች። በፍፁም ከባሏ የጠበቀችው ግምት አልነበረም።
«መናገር ነዋ! ሰው እንደዚህ ስትሆኚ ብዙ ነገር ሊገምት ይችላል። ሴት ልጅ ነሽ ምን ልገምት እችላለሁ ታዲያ?» ተቆጣ።
ከሪማ የሲሀምን እጅ እያሻሸች በረዥሙ ተነፈሰችና «ቀድመህ ገምተህ ነው እንጂ... ከእራት በኋላ እንድትነግርህ ተስማምተን ነበር። ሲሁዬ በቃ ማልቀሱ ይቅርና አስረጂው።» አለቻት።

መረገም ይሁን አሊያም መፈተን ግልፅ ባይሆንም ትውልዱ በማስመሰል ህይወት ውስጥ የሚዋልል ይመስላል። የቱ ጋ እንደተላለፈ እንጃ እንጂ ከራሱ እውነታ ጋር ተሸዋውዷል። ማንን እንደሚያታልል ባይታወቅም የሚፈልገው፣ የሚኖረውና የዓለም እውነታ ተዘበራርቆበታል። የዱኒያ ህይወት ካርታ ጠፍቶታል። የአኼራም ታንኳ ሸሽቶታል። በዚህ ከቀጠለ የሁለት ዓለም ኪሳራ... የሁለት ዓለም ውድቀት ሳያገኘው የሚቀር አይመስልም። ከዚህ በፊት... ከውድቀቱም ሆነ ከኪሳራው ማልዶ... ከራስ ጋር መታረቅ... ከእውነት ጋር መስማማት ያስፈልገዋል። እያመመው ቢሆንም ማስተካከል ከብዶታል። ደም እየተፋ ቢሆንም ራሱን ማከም ጠንቶታል። ወይ ይነቃል... ወይ ይሞታል።

እንባዋ የወለደውን ንፍጧን ከጠረጴዛው ላይ ሶፍት አንስታ ጠረገችና በፍርሀት ተመለከተችው። ለምን እንደፈራችው እሷም አታውቅም። ምናልባት ምርጫው ከሁለት መሀል ሆኖባት ይሆን? ሁለት ፅንፍ! መሀል የሌለው መልስ ይከብዳል።
«ጀም... ምን መሰለህ? የህክምና ተማሪ ነኝ አይደል? የህክምና ትምህርት ደግሞ እድሜ ይበላል። እና በጊዜ ማግባትና ህይወቴን ጎን ለጎን ማስኬድ እፈልጋለሁ።» በረዥሙ ተነፈሰች። ረዥም ዝምታ ተከተለ። ጀማል በግርምት ሲመለከታት ከቆየ በኋላ «እና ለዚህ ነው?» አለ።
«አዎ! ለዚህ ነው።» ወደ ኋላ ለጠጥ ብላ ተቀመጠች።
«ብታገቢ ደስ ይለናል እንጂ ... » ሳይጨርስ አቋረጠው። ለዚህ ስታለቅስ መቆየቷ አብሽቆታል። ከሪማ የሲሀምን ትከሻ አሸት እያደረገች «አብሽሪ ንገሪው!» አለቻት።
ሲሀም በረዥሙ ተንፍሳ ቀጠለች።
«እና የወደድኩት ሰው አለ። ማግባት እፈልጋለሁ። እሱም ሊያገባኝ ይፈልጋል። አባ ግን እንቢ አለኝ።»
«ለአባዬ ነገርሽው?»
አንገቷን በአዎንታ ነቀነቀችለት።
«ለምን እንቢ አለ? ለምን አልፈለገም?»
«ስራውን ጠየቀኝ ...»
«መጠየቁማ ትክክል ነው። በምን እንደሚያስተዳድርሽ ለማወቅ አስቦ ነው።»
«እሱ አልጠፋኝም። ስራውን ነገርኩት። አይሆንም አለ።»
«ምንድነው ስራው?»
«ጎበዝ ነጋዴ ነው። በደንብ ይሰራል።» አለችና የጀማል ፊት ላይ ስሜቱን ለማሰስ ሞከረች። ሙት ፊት ሆነባት። ይቀበለው ይጥላው መለየት አልቻለችም።
«እኔ ከወደድሽው ችግር የለብኝም ታውቂያለሽ! ግን ደግሞ የአባትሽን ባህሪ የምታጪው አይመስለኝም።»
«ስንተኛዬ ነው ስከለከል ጀማል? የኔስ ልብ? የኔስ መውደድ ምንም ዋጋ የለውም?» ከመቀመጫዋ ተስፈንጥራ ተነሳች። ከሪማ እንደምንም አቅፋ አስቀመጠቻት። መንሰቅሰቅ ጀመረች።
«ሴት ነኝ ጀማል! ሴት ነኝ! እድሜ ያልፈኛል። እጠወልጋለሁ። ተፈላጊነቴ ይቀንሳል! እንዴት አባ ባይረዳኝ አንተ ይጠፋሀል? እንዴት አትረዳኝም?»
«ከፈለግሽ ለምን አሁን አታገቢውም! አንቺ ከወደድሽው እኔ አልቃወምሽም። የራስሽን ጎጆ የምትቀልሺው አንቺ ነሽ! ግን አባትሽን መቼስ አትቆርጪውም። መፍትሔው ማለቃቀስ አይደለም። ልጁን አገናኚኝ ልተዋወቀው! ጥሩ ስነ ምግባር ካለው አባዬን አናግረዋለሁ።»
«አሁን የሶስተኛ አመት ተማሪ ነኝ። ከአራት አመት በኋላ ነው የምመረቀው... የሚፈልገኝ የምወደው ሰው የሚኖር ይመስልሀል? ልብም እኮ አስሬ መከፈት መዘጋት ያደክመዋል። ፍቅር ስጦታ ነው አስሬ አይገኝም። እያት ከሪማን.... እያት ሚስትህን! አንዴ ወደደችህ አገባችህ። እየው የእናንተን ህይወት! አላሳዝንህም እንዴ? እኔ እኮ እኩያዋ ነኝ። ስንት ልጅ አላችሁ አሁን? እኩያዬ ስንት ልጅ አላት? እኔ ገና አላገባሁም። ሴት ነኝ እኮ ጀማል! በአላህ አይንህን ከፍተህ ተመልከት! ህይወት የሌለው ዶክተርነት ምኔ ነው? እንዴት ነው እንደዚህ ተበጥብጬ ስኬታማስ የምሆነው? አግብቼ ብማር እኮ ሰላም አገኛለሁ። ምንም የሚበጠብጠኝ ነገር አይኖርም።»
«እሱ አልጠፋኝም። ለምን እኔ እምቢ ያልኩሽ ታስመስዪዋለሽ? አስተዋውቂኝ እሱን... የሚጠቅምሽ ከሆነ አባን አናግረዋለሁ ነው ያልኩት። የአቅሜን አደርጋለሁ። ውሳኔው የአባ ነው። ትናንት ተወልጄ የእርሱን ውሳኔ ማጠፍ አልችልም። ሀቁ የሱ ነው። መዳር የሚችለው እሱ ነው። እንደዛ ነው ያልኩት።»
መንሰቅሰቋ በረታ። መርገፍገፏ ጠነከረ። ረዳት አልባነት... አቅም የለሽነት ተሰማት።
«በጣም ሰልችቶኛል። በአላህ ሌጣነት ምርር ብሎኛል ከሪምዬ። የራሴንም የአፍቃሪዬንም ልብ መስበር መሮኛል።»
ከሪማ አቅፋ ለማባበል ትሞክራለች። ሬስቶራንቱ ውስጥ የተቀመጡት ሰዎች ዓይኖቻቸውን ከትሪያቸው ላይ አንስተው ወደ እነርሱ ወርውረዋል። ምናልባትም ምክንያቱን ለማወቅ እየገመቱ ይሆናል። የአንዲት ቆንጆ ሴት እንባ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ይሞክራሉ። ይበጇት ይመስል... በግርምትና በለምን ዓይን አሻግረው ይቃርማሉ።

‹‹ይገባኛል! ወጣት ነኝ … እረዳሻለሁ … ግን ደግሞ …›› አቋረጠችው፡፡
❤31
October 17, 2026 647 3