ዒድ ካከበርን በኋላ በሚመጣው እሁድ ዕለት የሚካሔደው ምርጫ ላይ፦ ንቁ ተሳትፎ ልናደርግ፣ ሰላማዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የበኩላችንን ልንወጣና የተሻለ ብለን ላሰብናቸው እጩዎች ድምጻችንን ልንሰጥ ይገባል። ዒደል-አድሓን ከቤተሰቦችና ከወዳጆች ጋር ለማክበር ወደ ክፍለ-ሐገር የሄዳችሁ ወንድሞችና እህቶች በዓሉን እንዳከበራችሁ በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የምርጫ ካርዳችሁ እንዳይባክንና ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ እንዲሁም መብታችሁን በአግባቡ እንድትጠቀሙ በከፍተኛ ሁኔታ አደራ ለማለት እንወዳለን። በአጭሩ፥ “እኔ ባልኖርም ሌላው ምርጫው ላይ ስለሚሳተፍ በቂ ነው” ከሚል ራስን የማዘናጊያ እሳቤ ልንርቅና በተቃራኒው “ሐላፊነት ከራስ ይጀምራል” ወደሚለው ተግባራዊ እርምጃ ልንሸጋገር ይገባል። ምርጫ ላይ መሳተፍ ግዴታ ባይሆንም መብትነቱን አውቀን ልንጠቀምበት ይገባል።
ሰባተኛው ጉዳይ የዒድ ፕሮግራም ለሚያዘጋጁ የሚድያ አካላት ሲሆን፥ ይህም
የዒድ በዓል ፕሮግራሞችን የምታስተላልፉ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ አካላት፣ በዒዱ እለት የምታስተላልፏቸው ፕሮግራሞችን ስታዘጋጁ የእስልምናን ሥነ-ምግባር ከሚያከብሩና ስለ ኢድ በትክክል ሕዝቡን ማስተማር ከሚችሉ ሰዎች መረጃ ይውሰዱ። የእስልምናን ሕግ የሚቃረኑ ተግባራት ከሚፈጽሙ ግለሰቦች ጋር በማያያዝ የእስልምናን ገጽታ የሚያበላሹ መልዕክቶችን አታስተላልፉ እንላለን።
ከሁሉ በላይ አስፈላጊው ጉዳይ፣ እንደ ኢስላማዊ ኃይማኖት ምሁራን አድርጋችሁ የምታቀርቧቸውን ሰዎች ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት (መጅሊስ) ጋር በመነጋገር ምርጫ ብታደርጉ ለኢስላም መልካም-ገጽታ ጥበቃ፣ ለፕሮግራማችሁ መሳካትና ለአድማጮችና ተመልካቾች ጥቅም አስተዋጽዖ የሚኖረው መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን። ስለኢስላም በቂ እውቀት የሌላቸውን ግለሰቦች በማቅረብ የምታዘጋጇቸው ፕሮግራሞች ላይ ስህተት ሊፈጠርና፣ ይህም የሙስሊሙን ማህበረሰብ ሊያስቆጣ እና የሚዲያችሁንም ስም ሊያጎድፍ ይችላል። እንደዚህ ያሉ ክስተቶች በተደጋጋሚ በበርካታ ሚድያዎች ላይ ተስተውለዋል።
በመጨረሻም፥ በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ በዒድ አስተባባሪ አብይ ኮሚቴና በራሴ ስም መልካም በአል እንዲሆንልን እመኛለሁ።
የአላህ እርዳታ ሁልጊዜም እንዳይለየን፣ አላህ በሁለቱም ሀገር ስኬታማ እንዲያደርገን፣ ሀገራችንንና ዓለሙን ከክፉ ነገር ሁሉ እንዲጠብቅልንና መልካም ነገሮችን እንዲለግሰን እንለምነዋለን፤ አሚን።
ዙል-ሒጃ 09/1447 ዓ.ሂ. / ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ል.
የዒድ አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ
አመሰግናለሁ።
7May 26, 2026 3.2K 1