ነሐሴ_፲፪ #ቅዱስ_ሚካኤል_ንጉሥ_ቆስጠንጢኖስን_ረደቶ_በድል_ያነገሠበት_ዕለት ንግሥት ዕሌኒም በ272ዓ.ም… — Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት — TG.ME

#ነሐሴ_፲፪
#ቅዱስ_ሚካኤል_ንጉሥ_ቆስጠንጢኖስን_ረደቶ_በድል_ያነገሠበት_ዕለት

ንግሥት ዕሌኒም በ272ዓ.ም ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት፤ ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱ የአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንደሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው የ፲፰ ዓመቱን ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፫፻ ዓ.ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሠራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ ነበር፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ፫፻፲፪ ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት "ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት" ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ በራእይ በሰማይ ላይ "በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ; የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ ለሠራዊቱ ሁሉ #የመስቀል_ምልክት በመሣሪያቸውና በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም #በቲቤር_ወንዝ_ድልድይ ላይ ጠላቱን ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ሆነ፡፡ ይኸውም የሆነው በመላእክት አለቃ #በቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ነው፡፡

#ሚካኤል ማለት #መኑ_ከመ_እግዚአብሔ "እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ለፍጥረታት ሁሉ የሚራዳና የሚያዝን የምሕረትና የመዳኛ፤ የሰላም መልአክ ነው፡፡ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› (ዳን.፲፪፥፩) በማለት በነቢዩ ዳንኤል የተነገረ ሲሆን በሌላ ቦታ ‹‹ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ›› (ዳን. ፲፥፲፫) በማለት ያስረዳል፡፡

በድርሳነ ሩፋኤል ላይ እንደተገለጸው ሰባት ሊቃነ መላእክት ቢኖሩም አለቃቸው #ቅዱስ_ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል አርምሞ ትዕግሥትን የሚወድ መልአክ ነው፡፡ ‹‹የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡››

ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር በተሰጠው ኃይል ዲያብሎስን ድል የነሣ መልአክ ነው፡፡ "በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡" ራእ ፲፪፥፯-፱፡፡

#ታላቁ_ቆስጠንጢኖስ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ከሆነ በኋላ በ፫፻ ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡

ንግሥት እሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም #የጌታችን_መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ፫፻፳፯ ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ #ቆስጠንጢኖስ_አምኖ በ፫፻፴፯ ዓ.ም #ተጠመቀ፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በጸሎቱ የምንታመን ሁላችንን የመልአክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን ረድኤት በረከቱን ያሳድርብን፡፡ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ስንክሳር ዘወርሃ ነሐሴ

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
❤10🙏4
August 18, 2026 1.5K 4