የኦርቶዶክሳዊ ሀገሩ የት ነው?
ጥያቄው የጅል ጥያቄ ይመስላል አይደል? አዎ ነው። ግን መልሱ እንደ ገደል የራቀ ነው። የመጣልን አልያ የሚመስለንን መመለስ መልስ ስለማይኾን ነው። መልሱን ለማግኘት ተግባሩን መከተል አግባብ ነው።
ኢትዮጵያ የኦርቶዶክሳዊነት ሃገር ናት። መሠረቷ የሕይወት ፍልስፍናዋ ተዋሕዶአዊነት ነው። ተከፍሎ ወይም ምንታዌነት የአውሮፓውያን የጥፋት ዘር በቅሎብን ነው። ሥጋና ነፍስን መነጣጠል፣ ሃይማኖትና ፓለቲካን ነጣጥሎ ማየት የኖረ ሳይኾን እንድንጠፋ የተዘራብን ነው። ሃገሩ የእኔ ነው። እኔ የዚኽ ሀገር ዜጋ ነኝ ካልክ በኋላ ፓለቲካው ግን አይመለከተኝም ካልኽ ደንቁረሃል ማለት ነው። ኑሮው መኖሪያው፣ መማሪያው ማምለኪያ ቦታው፣ ሥራው አይመለከተኝም ማለትኽ ነው። በጥቅሉ በገዛ እጅኽ ሃገሩን አስረክበሃል ማለት ነው።
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የኦርቶዶክሳዊ ሀገሩ የት ነው? ራሱ ኦርቶዶክሳዊው ስለ ሀገሩ የሚያስበው በጠላት የማሰቢያ መነጽርነት ነው። አንገቱ እየተቀላ በጥይት እየተደበደበ የሚሞተው ሃገርኽ አይደለም ቦታኽ አይደለኽም። ወራሪ ነኽ ሰፋሪ ነኽ እየተባለ ነው። ምድሪቱ ሀገሩቱ የእርሱ ኾና ሳለ በደምና አጥንት ቆጠራ መሬት ለክተው አንተ ከዚኽ ቦታ አይደለኽም ብለው ይገሉሃል።
ይኽንን ይዘን የጀርባ ሥነ ልቡናዊ የጥፋት ውቅሩንም እንየው።
በኦርቶዶክሳዊ መረዳት ሀገሩ የተከፋፈለው በሃገረ ስብከት እንጂ በብሔር አይደለም። ለዚኽ ነው ሃገረ ስብከት የምንለው። ስለዚኽ ፓለቲካው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣… ቢል ቤተ ክርስቲያን ይኽንን የምታውቀው በክልል ሳይኾን በሃገረ ስብከትነት ነው። ለስብከት የተከለለ ማለት ነው። አንድ ጳጳስ ለወንጌል ማዳረስ ይረዳው ዘንድ የተክልለለ ቦታ ወይም ሃገር ማለት ነው። ሃገረ ስብከት ዋና ዓላማው ለነስበክ ነው።
ኾኖም ግን የጠላት ወጥመድ ውስጥ ገብተን በትውልድ ስፍራ ላይ ጳጳስ መመደብ ጀመርን። ጎንደሬ ጎንደር፣ ሸዌ ሸዋ፣ ኦሮሞ ኦሮሚያ፣ ትግሬ ትግራይ ላይ። ይኽ አጥንትና ደም ቆጣሪ የዳርዊን ትምህርት እንጂ የኦርቶዶክሳዊ ትምህርት አይደለም። ለእኛ ክህደት ጭምር ነው።
የጎሳ አከላለል እውቀትም እውነትም የለውም። ትውልድን ሃገርን ከመበተን ውጭ ስሜትከመፍጠር ሌላ ሙያ የለውም። የተዋሐደውን በተነው።
ዘጠኙ ቅዱሳን ኢትዮጵያ ሃገረ ስብከታቸው ናት። ለአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ኢትዮጵያ ሀገረ ስብከታቸው ናት። ከደምና አጥንት ጋር አይያያዘም። እጨጌ እንባቆም ደብረ ሊባኖስ ሃገረ ስብከታቸው ናት። ኹሉም ፍሬ አፈሩበት።
የእኛ ጳጳሳት ወደ ሰፈራቸው የገቡት በምን ምክንያት ነው። ለስብከት ወይስ ለወንጀል መሸፈኛቸው? በደምና አጥንት ቆጠራ የተደበቁት ለስብከት ወይስ የፓለቲካ መስፈርት?
ዛሬ ኦርቶዶክሳዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገር የለውም። መጤ ኾኗል። ወለጋ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ ሐረር፣ ሶማሌ የሱ ሃገር አይደለም ተብሏል። ሃገረ ስብከት አለኝ የሚል ሲኖዶስ የሃገረ ስብከት ሉቀ ጳጳስ የስብከት ሃገሩን ወደ ጎሳ ክልል ሰጥቶ መንጎቹ ሲያልቁ ዝም ይላል።
በወለጋ በአርሲ የሚያልቁት ካህናት ምእመና ሃገረ ስብከታቸው ነው።
ኦርቶዶክሳዊ የሚኖረው በስብከት ሃገሩ ነው። ለዚኽ ነው ቤተ ክርስቲያን በኖረበት የሚተክለው። ዛሬ ግን ካለበት እየተነቀለ እንደ በግ እየታረደ የሚኖረው።
ይኽንን የሚያይ ጳጳስ ፣ ቄስ፣ ምእመናን ደግሞ በግድ የለሽነት እያዩ እየሰሙ ዝም ብለዋል። እንደ ሩቅ አካል ቆጥረዋቸዋል። ሕመማቸው አይሰማቸውም። ጳጳሱም የስብከት ሃገሩ ሳትኾን የሳንቲም ሃገሩ አድርጓታል። ወደ ስብከት ሃገራችን እንመለስ። ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ሃገር አይደለም። በሃገር መሞት እንዲያበቃ ሃገር የነጠቀንን መታገል ብቸኛው ምርጫ ነው። እመኑ የሰው ልጅ የማይተርፍባት የእልቂት ሃገር ከፊታን አለች። መኝታው በዝቷል፣ መዝለሉ ለንግሥ መደለቁ፣ ሕንጻ ግንባታው ቆሞ ስለ ሕዝብ ማትረፍ ብቻ እናስብ።
ንዋይ ካሳሁን
16
2August 26, 2026 2.9K 8