መከላከያ በሀብሩ ወረዳ በእሳት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ30 ሚሊዮን ብር እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME

መከላከያ በሀብሩ ወረዳ በእሳት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ30 ሚሊዮን ብር እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መስከረም 09 ቀን 2019 ዓ.ም

በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ 023 ቀጅማ ቀበሌ ቀሰማ ጎጥ በቅርቡ በደረሰ የእሳት አደጋ መኖሪያ ቤታቸዉ ሙሉ በሙሉ ለወደመባቸው ተጎጂዎች እና ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ የ30 ሚሊዮን ብር እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

​በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ሻምበል እመቤት ጌታቸው እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከተሰጠው ሀገራዊ ግዴታ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዓመቱን ሙሉ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

አሁንም በሀገራዊ የክረምት በጎ ፍቃድ መርሃ ግብር መሰረት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማቋቋም እና ዘላቂ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ 200 ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ እና በነፃነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

​የብልፅግና ፓርቲ የሰሜን ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የዞኑ የክረምት የዜጎች በጎ ፍቃድ አገልግሎት አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከድር ሙስጦፋ በበኩላቸው፤ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ላደረገው አርአያነት ያለው ድጋፍ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

​አደጋው የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክረምቱን በዳስ ውስጥ ማሳለፋቸውን የጠቆሙት አቶ ከድር፤ ከግሩፑ የተገኘውን 30 ሚሊዮን ብር እና ሌሎች ሀብቶችን በማስተባበር በሚቀጥሉት 45 ቀናት ውስጥ ቋሚ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማስረከብ ቦታ ተዘጋጅቶ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

​በመጨረሻም በዞኑ በርካታ ድጋፍ የሚሹ ተፈናቃዮች እና የችግር ሰለባዎች በመኖራቸው፣ ሌሎች ተቋማት፣ ግለሰቦች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይህንን በጎ አርአያ በመከተል ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ የድጋፍ ሥነ ሥርዓት ላይ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ፅህፈት ቤት ኃላፊን ጨምሮ ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተው ውድመት የደረሰበትን አካባቢ ተመልክተው ነዋሪዎችን አበረታትተዋል። ዘገባውን ያደረሰን የግሩፑ ፅህፈት ቤት ነው

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/

https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0

https://www.facebook.com/fdredefense.official
❤22👍14🔥1
September 19, 2026 2.8K 3