የዘርፉ የአምስት ዓመታት የልማት ጉዞ ሀገር አቀፍ ጉባኤ ነገ ይጀምራል
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የዘርፉን የአምስት ዓመታት የልማትና የሪፎርም ጉዞ በመገምገም፣ የቀጣይ የልማት ዘመን አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥበት ሀገር አቀፍ ጉባኤ ነገ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል።
ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ ሀገር አቀፍ መድረክ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑ ዋና ዋና የልማት ሥራዎች በጥልቀት ይገመገማሉ፤ በዘርፉ አንኳር ጉዳዮች ዙሪያም የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎን የክህሎት ኢትዮጵያ የሁለተኛው ዙር (2.0)ማጠቃለያ እና የቀጣዩ ዙር ይፋዊ ማብሰሪያ መርሃ ግብር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ይካሄዳል።
በኤክስፖው ሁለተኛው ዙር የክህሎት ኢትዮጵያ መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በመርሃ ግብሩ በታቀፉ ወጣቶች የተሰሩ፣ ችግር ፈቺ የሆኑና ወደ ምርትና አገልግሎት የተሸጋገሩ ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ ይቀርባሉ።
እንዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታት በተተገበረው የክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅጣጫ ውጤት ያመጡና ማሳያ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችና ሥራ ፈጣሪዎች፣ እንዲሁም የተመረጡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ።
ጉባኤው ያለፉትን አምስት ዓመታት የሚዘክር ብቻ ሳይሆን፣ የተገኙ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የቀጣይ ዘመን የሥራ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ፣ ክህሎትን ከሥራ፣ ከፈጠራ፣ ከቴክኖሎጂ እና ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር የሚያስተሳስር ሀገር አቀፍ መድረክ ነው።
በጉባኤው የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለድርሻና አጋር አካላት ተወካዮች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይሳተፋሉ።
ነሀሴ 24/2018 ዓ.ም፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ለወቅታዊ ትኩስ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
Official Website: mols.gov.et
Facebook: https://web.facebook.com/MolsFDRE
Telegram: https://t.me/FDRE_MoLSofficial
TikTok: tiktok.com/@mols_official
Twitter / X: twitter.com/Jobs_ሚኒስቴር
WhatsApp: whatsapp.com/channel/0029VakCgcYI



