ሃይኒከን ኢትዮጵያ የ15 ዓመት ጉዞውን አከበረ
#FastMereja I የዓለማችን ታዋቂው የቢራ አምራች ሃይኒከን በኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረውን የ15 ዓመት የኢንቨስትመንት እና አጋርነት ጉዞ “15 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ማደግ” በሚል መሪ ቃል በቂሊንጦ ቢራ ፋብሪካው ባካሄደው ስነ-ስርዓት አከበረ።
በክብረ በዓሉ ላይ የመንግስት ሃላፊዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ሰራተኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ኩባንያው ባለፉት 15 ዓመታት ከ1 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስት በማድረግ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እድገት ላይ ያበረከተው አስተዋጽኦ ተዘክሯል።
የሃይኒከን ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ባርት ዲ ኬኒንክ እንደገለጹት፣ ኩባንያው በ2003 ዓ.ም የሐረር እና የበደሌ ቢራ ፋብሪካዎችን በመግዛት እንዲሁም በቂሊንጦ ዘመናዊ ፋብሪካ በመገንባት እንቅስቃሴውን የጀመረ ሲሆን፣ ላለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት የሀገሪቱ ከፍተኛ የግል ግብር ከፋይ በመሆን ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አድርጓል።
በግብርናው ዘርፍ እ.ኤ.አ. በ2011 በ2,500 አርሶ አደሮች የተጀመረው የገብስ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት ከ120,000 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ ከ2023 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ (100%) ሀገር በቀል ገብስ በመጠቀም ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል።
በተጨማሪም ኩባንያው በቀጥታ እና በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ከ137,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ በቡርቃ እና ደራሽ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከ82,000 በላይ ሰዎችን የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ እና 7,400 ሄክታር መሬት በማልማት ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክሏል።
ኩባንያው የቂሊንጦ ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀም በማድረግ በካርቦን ነፃ አሰራር ቀዳሚ ለመሆን ትልቅ ኢንቨስትመንት ማድረጉን ይፋ አድርጓል።
በመጨረሻም በ15 አመት ጉዞ አጋር የነበሩ ተቋማትን እውቅና ሰጥቷል።
4September 1, 2026 1.3K 1