ኢንስቲትዩቱ በሥርዓተ-ፆታ ክትትልና ግምገማ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው
------------------------
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከቤልጂየሙ የትሮፒካል ሜዲሲን ኢንስቲትዩት (ITM) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሶስት ቀን የሥርዓተ-ፆታ ክትትልና ግምገማ መገልገያ (Gender Monitoring and Evaluation Tool) ለማበልጸግ የምክክርና የሥልጠና መድረክ ከነሐሴ 12/ 2018 ዓ.ም ማካሄድ ጀምሯል።
የምክክር መድረኩ በጤና ምርምርና ፕሮግራሞች ውስጥ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን በተጨባጭ ማካተት የሚያስችልና የአጋር ተቋማቱን የጋራ መግባባት መሠረት ያደረገ የመከታተያና መገምገሚያ መሣሪያ (M&E Tool) በጋራ ማበልጸግ ያለመ ነው።
የኢንስቲትዩቱ የሴቶችና ማህበራዊ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ የሮም ሞረዳ እንደገለፁት ስልጠናዉ ከኢንስቲትዩት
ከጅማ፣ ከጎንደር፣ ከአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ፣ እንዲሁም ከክልል የተውጣጡ የመስኩ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት የሚገኙ ሲሆን፣ ስርዓተ ጾታ ላይ የሚሰሩ አጠቃላይ ስራዎች ላይ እና ፕሮጀክቱ ላይ በመስራት ላይ ያሉ ተቋማትም በስልጠናው ይካተታሉ።
የኢንስቲትዩቱ የወባና ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይርከቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰዉ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ይህ መሳሪያ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ተቋማት በፕሮግራሞች ዕቅድ፣ አፈጻጸምና ግምገማ ውስጥ በቀጥታ ማካተት የሚያስችላቸው በመሆኑ፤ ተቋማቱ ውጤታማ የክትትል ሥርዓት እንዲዘረጉ ያስችላቸዋል።
በመድረኩ በከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት የሚታዩ የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቶች የሚዳሰሱ ሲሆን፤ በተግባር ላይ የሚውሉ የመከታተያ አመላካቾች (Indicators) ተቀርጸው ለተግባራዊነታቸው አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
https://ephi.gov.et/ኢንስቲትዩቱ-የሥርዓተ-ፆታ-ክትትልና-ግም/
https://www.facebook.com/share/p/194kB4Uu6x/
https://x.com/i/status/2090076407204356289
August 19, 2026 3.9K 2