የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ዘርፍ ሪፎርምን በተግባር ለማስፈጸም የጋራ ግንዛቤ ፈጠረ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ዘርፍ ሪፎርምን በተመለከተ ለኢንስቲትዩቱ አመራርና ሠራተኞች የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የጤና ዘርፍ ሪፎርሙ የዝግጅት፣ የትግበራ፣ የማፅናትና የኢንተርፕሬነርሺፕ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር የጤና ሥርዓቱን የበለጠ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ ለማድረግ የታቀደ መሆኑ የገለፁት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የጤና ዘርፍ ሪፎርሙ የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን፣ ያሉ ክፍተቶችን ለይቶ ለመሙላትና ተቋማት ከዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት ጋር ተጣጥመው ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዶ/ር መሳይ ሠራተኞች የሥራ ዝርዝራቸውንና የብቃት መስፈርታቸውን በግልጽ በመረዳት ለሚመጣው የብቃት ምዘና መዘጋጀት፣ ከአሉቧልታ ይልቅ ትክክለኛ መረጃን መከተልና ሪፎርሙን በጋራ በመረዳት በተግባር ማስፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ብቃትና አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ደምሴ ሰነዱን ሲያቀርቡ፣ የሪፎርሙን የብቃት ማዕቀፍ፣ የሥራ ዝርዝርና የዲጂታል እና መሶብ አገልግሎቶች አቅጣጫዎችን አብራርተዋል።
በመድረኩ የሪፎርሙ ዋና ዓላማ የጤና አገልግሎትን ማሻሻል፣ ብቃት ያለውና ተነሳሽነት ያለው የጤና ዘርፍ የሰው ኃይል መገንባት፣ የጤና ዲጂታላይዜሽንን ማጠናከር፣ ሀገር በቀል የጤና ግብዓቶችን ማሳደግና ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በማሳለጥ የጤና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ሠራተኞች ያነሷቸውን ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችና ጥያቄዎች በተመለከተ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል። ይህም በሪፎርሙ ዓላማ፣ አቅጣጫ፣ ትግበራና በሠራተኞች ሚና ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር አስችሏል።
በመጨረሻም እስካሁን የተገኙ ስኬቶችን በማፅናት፣ የተቋማዊ አሠራርንና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማጠናከር፣ ብቃትን፣ ጥራትን፣ ብዝሃነትንና አካታችነትን በማስቀደም የሪፎርሙን ዓላማ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የኢንስቲትዩቱ አመራርና ሠራተኞች የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገልጿል።
August 14, 2026 3.7K 4