የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ 12.8 በመቶ ወይም 70, 544 ተማሪዎች የማለፊያ ወጤት ማምጣታቸው ተገለጸ። በዘንድሮው ፈተና ከ600 ከፍተኛ ውጤት 591.64 በተፈጥሮ ሳይንስ ሆኖ ተመዝግቧል። ----------------------------- // ------------------------------- (ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም) የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ 12.8 በመቶ ወይም 70, 544 ተማሪዎች 50% እና በላይ ወጤት ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል። ባለፈው ዓመት በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 8.9 በመቶ ተማሪዎች ማለፋቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህ ዓመት የማለፊያውን ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከ20 ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ 16.58 በመቶ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 8.33 በመቶ መሆኑንም ተናግረዋል። በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 ከፍተኛ ውጤት 591.64 በወንድ ፤ 583.03 በሴት ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ከ600 ከፍተኛ በወንድ 576.25 በሴት 569.17 ሆኖ መመዝገቡን አብራርተዋል። በዚህ ዓመት ተማሪዎችን ካስፈተኑ ት/ቤቶች መካከል 88 ት/ቤቶች 100% ተማሪዎቻቸውን ማሳለፋቸውን እና 565 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ምንም ተማሪ አለማሳለፋቸውን ተናግረው ከባለፈው ዓመት ምንም ካላሳለፉ 1232 ት/ቤቶች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ለፈተና ከተመዘገቡ 563,960 ተማሪዎች ውስጥ 550,210 ተማሪዎች ፈተናቸውን ወስደዋል። በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ እየነተገበሩ ባሉ የሪፎርም እርምጃዎች የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የዘንድሮው ውጤት ማሳያ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
22
7
3