የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን/contract signing date/ እና በኮንስትራክሽን ውል የስራ… — Ethio Construction Engineering — TG.ME

👉የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን/contract signing date/ እና በኮንስትራክሽን ውል የስራ መጀመሪያ ቀን/Commencement date/.

በኮንስትራክሽን ውል ውስጥ የስራ መጀመሪያ ቀን እና ውል የተደረገበት ቀን የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ይሄውም የሆነበት ውሉ በተደረገበት እለት የግንባታ ስራ ይጀመራል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፡፡

*በኮንስትራክሽን ውል የስራ መጀመሪያ ቀን/Commencement date/

በመርህ ደረጃ የውል የግንባታ ስራ ማከናወኛ የጊዜ ገደብ መቆጠር የሚጀምረው ከኮመንስመንት ዴት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ የውሉ የግንባታ ጊዜ ተብሎ የሚጠቀሰውን ቀን ውሉ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ መቁጠር ስህተት ነው፡፡

ምክንያቱም የኮንስትራክሽን ውል በአሰሪና ተቋራጭ መካከል ከተፈረመ በኋላ የግንባታው ተጨባጭ ስራ በተለያየ ምክንያት ሊዘገይ ይችላል፡፡ለምሳሌ ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ የይገባኛል ጭቅጭቅ ቢነሳበት ጭቅጭቁ እስኪፈታ ድረስ አሰሪው የግንባታውን ሳይት ለተቋራጩ ማስረከብ ያልቻለ እንደሆነ ግንባታው ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ ሳይጀመር መቆየቱ የማይቀር ይሆናል፡፡

*ለተቋራጩ የሳይት ርክክብ/site handover/

ለግንባታ የተወሰነው ቦታ ከጥያቄ ነጻ ከሆነና አሰሪው ሙሉ ባለይዞታ ለመሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ፤ ውል ላዋዋለው ሥራ ተቋራጭ የሥራ ቦታውን ያስረክባል ወይም የሳይት ርክክብ ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡

ይህ ከሆነ በኋላ አሰሪው ሥራ ተቋራጩ የግንባታ ሥራውን የሚጀምርበትን ቀን
- በርክክብ ወቅት በቃለ ጉባዔ ይወስናል፡፡
- ወይም አስቀድሞ በውሉ ልዩ ሁኔታዎች(Special condition of contract) ላይ በተቀመጠው ቀን እንደሆነ ታውቆ በተባለው ቀን ሥራ ይጀመራለረ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ሥራ ተቋራጩ ሳይት ሳይረከብ የግንባታው ጅማሬ ቀን ሊቆጠር አይችልም ማለት ነው፡፡
ሳይት ርክክብ ከተደረገ በኋላ እንደፕሮጀክቱ ዓይነት ወይም መጠን ስፋት የሞቢላይዜሽን ቀን ተጨምሮ ዋና የግንባታ ሥራ ማስጀመሪያው ቀን ይወሰናል፡፡ ስለዚህ ተቋራጩ የግንባታ ቁሳቁስ እና የሰው ሀይል ሞቢላይዝ እስከሚያደርግበት ምክንያታዊ ጊዜ ድረስ የስራ መጀመሪያ ቀን ሊጀምርበት አይገባም፡፡

በዚህ ረገድ በተግባር አልፎ አልፎ ስህተት ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ይሄውም አሰሪዎች አንዳንዴ የግንባታውን ጊዜ ውሉ ከተደረገበት ቀን ጀምረው በመቁጠር እና ተቋራጩን በቂ ምክንያት ካለህ የጊዜ ማራዘሚያ/Time extension/ ጠይቅ የሚሉበት የተሳሳተ ሁኔታና አጋጣሚ አለ፡፡

በዚህ ረገድ በሀገራችን እና በአለም ሀገራት እየተሰራባቸው ያሉ የዳበሩ የፊዲክ ጀኔራል ኮንዲሽኖች እና በሀገራችን ተጣጥመው የተቀረጹ ጀኔራል ኮንዲሽኖች ምን ይዘት አላቸው የሚለውን እና የፍትሀብሄር ህግ ድንጋጌዎችን ደግሞ ቀጥለን እንዳስሳለን፡፡

1. FIDIC RED BOOK 1999

በፊዲክ ሬድ ቡክ 1999 ቨርሽን ክሎስ 8.1 ላይ ኢንጅኒየሩ ለተቋራጩ ስራ እንዲጀምር ማስታወቅ እንዳለበት እና ከ7 ቀን ያላነሰ ጊዜ መስጠት እንደሚገባው ይጠቅሳል፡፡

እንደዚሁም በስፔሻል ኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት በልዩ ሁኔታ ካልተቀመጠ በስተቀር የስራ መጀመሪያው ቀን/ Commencement date/ ተቋራጩ በጨረታው አሸናፊነቱ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ በ42 ቀናት ውስጥ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል፡፡

በተጨማሪም ተቋራጩ ከስራ መጀመሪያ ቀን በኋላ ወዲያውኑ እና ያለመዘግየት የግንባታ ስራ መጀመር እንዳለበት ይገልጻል፡፡ተቋራጩ/contractor/ ከስራ መጀመሪያ ቀን በኋላ ይቅርታ ሊያሰጥ የሚችል ምክንያት ሳይኖረው ያለመዘግየት የግንባታ ስራ መጀመር እንዳለበት በክሎስ ላይ የተቀመጠውን ግዴታውን ያልተወጣ እንደሆነ ደግሞ አሰሪው/client/ውሉን ለማቋረጥ እንደሚችል ክሎስ 15.2(c) ላይ ተቀምጧል

2. FIDIC 1987

በኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት ፎር ወርክስ ኦፍ ሲቪል ኢንጅነረንግ ኮንስትራክሽን ፊዲክ 1987 ቨርሽን ክሎስ 41.1 ላይ ስለ ኮመንስመንት ዴት/የስራ መጀመሪያ ቀን ተቀምጧል፡፡ይዘቱም መሀንዲሱ የስራ መጀመሪያውን ቀን በጨረታ ሰነዱ አፔንዴክስ ላይ በተገለጸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለተቋራጩ ማስታወቅ እንዳለበት የሚገልጽ ነው፡፡ተቋራጩም የስራ መጀመሪያው ቀን በመሀንዲሱ ከተገለጸለት በኋላ ያለመዘግየት እና በተቻለ ፍጥነት የግንባታ ስራውን መጀመር እንዳለበት ይገልጻል፡፡

የግንባታ ማጠናቀቂያ ቀን/completion date/ መቆጠር የሚጀምረውም ከኮመንስመንት ዴት ጀምሮ ስለመሆኑ ክሎስ 43.1 ላይ ተቀምጧል፡፡

እንግዲህ ተቋራጩ በቂ ምክንያት ሳይኖረው በክሎስ 41.1 ላይ በተመለከተው አግባብ የግንባታ ስራውን ሳይጀምር የቀረ እንደሆነ አሰሪው የ14 ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን ለማቋረጥ እና ተቋራጩን ከሳይት ለማስወጣት መብት/expel right/ እንዳለው ክሎስ 63.1 ያስቀምጣል፡፡

3. የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር  አቋም/MoWUD 1994

ይህ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ1994 ስራ ላይ አውሎት የነበረው የሲቪል ግንባታ ስራዎች ቋሚ የውል መተዳደሪያ/MoWUD 1994 በተለይ ከፊዲክ/FIDIC 1987 ቨርሽን የተወሰደ ሲሆን ስለኮመንስመንት ዴት በሁለቱም ጀኔራል ኮንዲሽኖች ላይ ተመሳሳይ ይዘት ባለው ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡
ስለዚህ ማብራሪያውን መድገም አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡

4. የመንግስት ግዢዎች ኤጀንሲ/PPA 2011

በፒፒኤ 2011 ቨርሽን ክሎስ 71 ላይ የስራ መጀመሪያ ቀን በስፔሻል ኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት ላይ ሊቀመጥ እንደሚችል ወይም ደግሞ በአስተዳደራዊ መንገድ በኢንጅኒየሩ በሚሰጥ ትእዛዝ ሊታወቅ እንደሚችል ይጠቅሳል፡፡

እንዲሁም በሌላ ሁኔታ በውሉ ላይ ካልተገለጸ በስተቀር ለተቋራጩ የጨረታ አሸናፊነቱ ከተገለጸ ቀን ጀምሮ ታስቦ ከ120 ቀናት ለማለፍ አይችልም፡፡

5-የፍትሀብሄር ህግ

የስራ ማከናወኛ ውል(የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 2610 - 2637) በሚመለከት በውሉ ላይ የጊዜ ጉዳይ በግልጽ ያልተጠቀሰ እንደሆነ ተቋራጩ ወዲያውኑ ስራ መጀመር እንደሚኖርበት በአንቀጽ 2619 ላይ ተደንግጓል፡፡የግንባታ ጊዜ በተገለጸባቸው ውሎች ደግሞ ስራ ተቋራጩ ስራውን ወዲያው ያልጀመረ እንደሆነ እና በጊዜ ገደቡ የግንባታ ስራውን ለመፈጸም የማይችል መሆኑ የታወቀ እንደሆነ አሰሪው ለተቋራጩ ስራውን የሚጀምርበትን ጊዜ ሊወስንለት እንደሚችል በአንቀጽ 2618 ላይ ተቀምጧል፡፡

ሌላው እነዚህ ደንቦች ስለማይንቀሳቀስ ንብረት ስራ ውል(የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3019-3040) በሚመለከተው የግል የስራ ተቋራጭነት ውል ላይ ጭምር ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው ከአንቀጽ 3019(2) ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የአስተዳደር መስሪያ ቤት የኮንስትራክሽን ውል ማለትም የመንግስት ስራዎች መቋረጥ ውል(የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3244 እና ተከታዮቹ) በሚመለከት እያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን ግዴታዎቹን በውሉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ መፈጸም ይኖርበታል፡፡

በውሉ ላይ ግልጽ የጊዜ ስምምነት የሌለ እንደሆነ ደግሞ ግዴታው በአእምሮ ግምት በቂ በሆነ ጊዜ መፈጸም እንደሚኖርበት በአንቀጽ 3174 ላይ ተቀምጧል፡፡

ይህ ድንጋጌ ስለአስተዳደር መስሪያ ቤት ውሎች በጠቅላላው የተደነገገ ሲሆን የመንግስት ስራዎች መቋረጥ ውልን በሚመለከተው ልዩ ክፍል ላይም በግልጽ ስለስራ ጊዜ ተደንግጓል፡፡

@etconp
❤8👍3
August 27, 2026 3.1K 58