EFF Refereeing Departement (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ዲፖርትመንት): post #592 — TG.ME

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ይፋዊ መግለጫ የቀድሞ አንጋፋ የዳኝነት ሙያተኞችን በማክበር እውቅና ሰጠ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ በሀገራችን የዳኝነት ሙያ ላይ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ፣ ለፈፀሙት ታላቅ አገልግሎት እና ለሙያው እድገት ላበረከቱት ዘላቂ አሻራ ለሁለት አንጋፋ የቀድሞ የዳኝነት ሙያተኞች ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ እና ኃይለመላክ ተሰማ እውቅና ሰጥቷል። በዳኝነት ሙያ ለብዙ ዓመታት በታማኝነት፣ በሙያዊ ብቃት እና በከፍተኛ ቁርጠኝነት ያገለገሉት እነዚህ አንጋፋ ባለሙያዎች የዳኝነት ሙያን በማሳደግ፣ የተሻለ የዳኝነት ባህል በመገንባት እና ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ በመሆን የማይረሱ አስተዋፅኦዎችን አበርክተዋል። የብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ እንደሚያምነው፣ ለሙያው ያደሩ እና ታሪካዊ አሻራ ያሳረፉ ባለሙያዎችን ማክበርና እውቅና መስጠት ያለፈውን ትውልድ ለማመስገን ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ላሉ ዳኞች እና ወደፊት ወደ ሙያው ለሚመጡ ወጣት ተስፈኞች ትልቅ ተነሳሽነትና ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው። ይህ የእውቅና አሰጣጥ በዳኝነት ሙያ ውስጥ አንጋፋ ባለሙያዎችን የማክበር ባህል በቀጣይም ለሙያው የማይረሳ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን በመለየት ተመሳሳይ የእውቅና መስጠት ሂደት እንደሚቀጥል ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ያስታውቃል። ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ለሁሉም የቀድሞ እና አሁን ያሉ ዳኞች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋናውን ያቀርባል። የዳኝነት ሙያን በጋራ ጥረት፣ በሙያዊ እሴት እና በተጠያቂነት የበለጠ ለማሳደግ ቁርጠኝነቱን ይገልጻል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ

July 23, 2026 2.1K 4