ከአረብ ሀገራት ለተመለሱ ዜጎች የሥራ ፈጠራ ሥልጠና በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰጠት ተጀመረ፡፡…

ከአረብ ሀገራት ለተመለሱ ዜጎች የሥራ ፈጠራ ሥልጠና በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰጠት ተጀመረ፡፡

ደብረ ብርሃን፣ ህዳር 03/2019 ዓ.ም

በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) እና በደብረ ብርሃን ሥራና ክህሎት መምሪያ እና በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስተባባሪነት ከአረብ ሀገራት ለተመለሱ ዜጎች የኢንተርፕረነርሺፕ (የሥራ ፈጠራ) ሥልጠና በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰጠት ተጀመረ።

የሥልጠናው ዋና ዓላማ ከአረብ ሀገራት የተመለሱ ዜጎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ፣ ከተረጂነት ተላቀው ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ እንዲሁም ለሥራ ፈጠራ የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያጎለብቱ ማስቻል ነው።

በሥልጠናው ወቅት ተመላሽ ዜጎች በውጭ ሀገር ያካበቱትን የሥራ ልምድ ከኮሌጁ በሚያገኙት አዲስ የሥራ ፈጠራ ዕውቀት ጋር በማቀናጀት ወደ ተግባራዊ ሥራ እንዲሸጋገሩ የተቀናጀ አመራርና ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በተጨማሪም ለሥራ ፈጠራ የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ለማመቻቸት ታስቧል።

የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ባሻዬ በየነ በሰጡት ማብራሪያ ሥልጠናው በኮሌጁ ለሦስት ቀናት እንደሚሰጥ ገልጸዋል። አቶ ባሻዬ አክለውም ሥልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ የንግድ ባንክ የሰሜን ምስራቅ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ በመገኘት ስለ ብድር አሰጣጥ፣ አመላለስና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ሰልጣኞች በሥልጠናው ሙሉ በሙሉ መሳተፍ፣ የተሰጣቸውን ትምህርት በትክክል መከታተልና ማስታወሻ በመያዝ በትጋት መማር እንዳለባቸው አሳስበዋል። የሥልጠናውን መስፈርት በሚያሟሉና በተገቢው ሁኔታ በሚሳተፉ ሰልጣኞች ላይ ተመሥርቶ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

ይህ የሥልጠና ፕሮግራም ተመላሽ ዜጎች ያላቸውን የሥራ ልምድ ወደ ራሳቸው የኢኮኖሚ እድገት በመቀየር የሥራ ዕድል ፈጣሪና ምርታማ ዜጎች እንዲሆኑ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

#ደብር ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ህዝብ ግንኙነት
❤9
November 12, 2026 1.2K