ተመጋጋቢ ማኑፋክቸሪንግ እያስፋፋን ነው» - የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተለያዩ የአምራቾች እና ኢንዱስትሪዎች… — Development Bank of Ethiopia (DBE) — TG.ME

«ተመጋጋቢ ማኑፋክቸሪንግ እያስፋፋን ነው» - የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

የተለያዩ የአምራቾች እና ኢንዱስትሪዎች የምርት ሂደት፣ ግብዓት እና ተረፈ-ምርትን በመካፈል እርስ በእርስ ተደጋገፌውና ተጣጥመው የሚሠሩበት የኢንዱስትሪ አመራረት ሥርዓት ተመጋጋቢ ማኑፋክቸሪንግ ይሰኛል፡፡

እሳቤው በዋናነት የእሴት ሰንሰለት  ያጠናክራል፡፡ ሂደቱ በሀገር ውስጥ ባሉ አምራቾች መካከል ጠንካራ የንግድ ትስስር ስለሚፈጥር የውጭ ገበያ ድንገተኛ መናጋት ቢገጥመው እንኳ ኢንዱስትሪዎች እንዳይወድቁ ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይህን የኢንዱስትሪ ሥርዓት ለረጅም ጊዜ ፋይናንስ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ «ዴዴ» የጠርሙስ ፋብሪካ ደግሞ የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባው ፋብሪካው በዓመት 164 ሚሊየን የምግብ ማሸጊያ ጠርሙሶችን ያመርታል፡፡

ፋብሪካው ተመጋጋቢ የማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ሥርዓት ማሳያ ስለመሆኑ አቶ ጌታሰው ፈንታው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው የባንኩ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ እና ብራንች ባንኪንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡

ኳርትዝ አሸዋ (Quartz Sand / Silica Sand) የጠርሙስ ምርት ዋነኛው ግብዓት ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ጠርሙስ ከ60 – 70 ከመቶው ኳርትዝ አሸዋ ነው እንደማለት፡፡ ይህ ጥሬ ዕቃ ደግሞ ከደብረ ብርሃን ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ለሚ ከተማ ለፋብሪካው ይቀርባል፡፡

የጠርሙስ ጥንካሬ እና ዘላቂነት የሚጨምር እምነበረድ (ላይምስቶን) እና የመስታወቱን ቅርፅ የመያዝ አቅም የሚያስተካክል ግብዓት ዶሎማይት ደግሞ እዚሁ ሀገራችን የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች ናቸው፡፡

ይህም የማዕድን ዘርፍ አልሚዎች እና የጠርሙስ አምራች ኩባንያዎች ተመጋጋቢነት ውጤት ስለመሆኑ አቶ ጌታሰው አስምረውበታል፡፡

ውጤቱም የሎጂስቲክስ ወጪን ቀንሷል፣ የውጭ ምንዛሬን አድኗል፣ የኢንዱስትሪዎችን አጠቃላይ ምርታማነት እና የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ ችሏል፡፡

ጥቅም ላይ የዋሉ እና ያረጁ ጠርሙሶች እና መስታወቶች (Cullet / Recycled Glass) ለጠርሙስ ምርት ተጨማሪ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ይህን በማሰባሰብ የሚያቀርቡት የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው፡፡ አሰራሩ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለአካባቢ ጥበቃም የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አስምረውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተመጋጋቢ ማኑፋክቸሪንግ እሳቤን  በተግባር ፋይናንስ አድርጓል ያሉት አቶ ጌታሰው፤ ግብዓት የሚያቀርብ፣ ምርት የሚወስድ እና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ተዋናዮች በተፈጠረው የገበያ ሰንሰለት  እንዲሰሩ አስችሏል፤  ድምር ውጤቱ የላቀ ነው ብለዋል፡፡

በዚሁ እሳቤ መሠረት ልማት ባንክ ፋይናንስ ያደረገው «ዴዴ» የጠርሙስ ፋብሪካ ከተመጋጋቢ ማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ አመራረት ሥርዓት እድገት በተጨማሪ  ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የጠርሙስ ፍላጎት 62 ከመቶውን መሸፈን የሚችል ነው፡፡
👍9❤2
September 2, 2026 1.9K 2