Development Bank of Ethiopia (DBE): post #3100 — TG.ME

ከሀገር ለ ሀገር..
ጎበዝ ባለሙያ እና ስራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ፋርማሲስት ነው። ከጊዜ በኋላ የሕክምና መድኃኒቶች አስመጪ ሆነ። ይህ ደግሞ ሁለት ጥቅሞች አሉት፦ ከፈጣሪ በታች ለሕሙማን ፈውስ መሆን እና የሥራው አዋጭነት።
ያም ሆኖ በተሳካ ቢዝነስ ውስጥ ፋርማሲስቱን እረፍት የሚነሳው ነጥብ ነበር። ሀገሪቱ 85 ከመቶ የሚሆነውን የሕክምና መድኃኒት ፍላጎቷን ከውጭ ታስገባለች የሚለው አኃዛዊ መረጃ የፋርማሲስቱ የእረፍት እጦት ማጠንጠኛ ሆነ።
ግዙፍ የመድኃኒት ፋብሪካዎች እያሉ የፍላጎት እና የአቅርቦት መጠን አለመጣጣም ለወጣቱ ባለሙያ በእርግጥም መመለስ የነበረበት ጥያቄ ነበር።
ባለሙያው ለጥያቄው መልስ ሲያፈላልግ «ለምን?»፣ «እንዴት?»፣ «በምን?» እና «ለማን?» የሚሉት ተጠየቆች ደረጃ በደረጃ መልክና ቅርፅ እየያዙ መጡ።
ዘርፉን መለየት ቀዳሚው ተግባር ነበር። እንደ ሀገር ከውጭ ከሚገባው የሕክምና መድኃኒት እስከ 15 በመቶ የሚሆነው የቆዳ ሕክምና መድኃኒቶች ናቸው። የቆዳ ሕክምና መድኃኒቶችን ብቻ ለይቶ የሚያመርት ተቋም አለመኖሩም ታወቀ።
ፋርማሲስቱ ይህን ጉዳይ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በቁም ነገር መከረበት፤ ለቆዳ ሕክምና የሚውል ቅባት የሚያመርት ፋብሪካ መትከል የሚለው ሀሳብ ተወለደ።
ሀገር በልጆቿ የሚበረከትላት ይህ ፋብሪካ መጠሪያው «ትረስት ፋርማሲዩቲካልስ ማኑፋክቸሪንግ» ሆነ። ተገቢው የወረቀት ሥራ በጥልቀት ተከወነ። ሆኖም ፋብሪካውን እውን ለማድረግ ቢሊዮናት ያስፈልጉ ነበር።
የገበያ ክፍተትን የሚፈታ፣ የፖሊሲ ትኩረት ያለው እና የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንትን ፋይናንስ የሚያደርገው ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብቻ ነው።
ፋርማሲስቱ እና አጋሮቹ ወደ አንጋፋው ልማት ባንክ ጎራ አሉ፤ ተገቢው አቀባበል ተደረገላቸው። እቅዳቸው ጥብቅ የሆነውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፕሮጀክት ፋይዳ፣ አተገባበር፣ አዋጭነት እና ተያያዥ መስፈርቶች አልፎ በፕሮጀክት ፋይናሲንግ ተካተተ፡፡
ይህ የፋርማሲስት ሄኖክ ተካ ሀሳብ አሁን ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ ግዘፍ ነስቷል።
ትረስት ፋርማሲዩቲካልስ ማኑፋክቸሪንግ በ31,544 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ቅጥሩን አስከብሯል። ከዚህ ውስጥ መድኃኒት የሚያመርተው ፋብሪካ ብቻ በ3,200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባረፈ ባለ አንድ ወለል ሕንፃ ላይ ተገንብቷል።
የትኛውንም ዓይነት በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ፍጹም በሚከላከል ቴክኖሎጂ እና ዲዛይን የተገነባው ፋብሪካው ማሽነሪዎችን ተክሎ ጨርሷል።
ፋብሪካው በፈንገስ፣ በባክቴሪያ እና በአለርጂ የሚመጡ የቆዳ በሽታዎችንና ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚውሉ ሦስት ዋና ዋና የቆዳ ሕክምና ቅባቶችን (Dermatological Ointments & Creams)፣ ሻምፖ እና ሎሽን ያመርታል።
ለሕፃናት ሕመም ማስታገሻ የሚሆን ሳፖዚተሪ (በፊንጣጣ በኩል የሚወሰድ የትኩሳትና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት) ሌላኛው የፋብሪካው ምርት ነው።
በዓመት 158 ሚሊዮን ቲዩብ አይንትመንት እና ክሬም የማምረት አቅም አለው። ይህም ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነፍስ ወከፍ አንድ ምርት ይደረስዋል አንደማት ማለት ።
ይህም ከውጭ የሚገቡትን የቆዳ ሕክምና ቅባቶች ሙሉ በሙሉ ያስቀራል፤ የዋጋ መረጋጋት ይፈጥራል፤ ከፍተኛ ሽፋን እና ተዳራሽነት እንዲኖር ማድረግ እና ለፋርማሲዩቲካል ዘርፉ የላቀ እድገት መፍጠር የዚህ ፋብሪካ ገጸ-በረከቶች ናቸው።
በአንድ ሽፍት ብቻ ለ170 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥረው ትረስት ፋርማሲዩቲካልስ ማኑፋክቸሪንግ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ድፍን አፍሪካን በገበያ የመድረስ እቅድም አቅምም ፈጥሯል። ፋብሪካው ከዲዛይኑ ጀምሮ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅትን መስፈርቶች ጠብቋል፡፡
በቀጣይ አምስት ወራት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ትረስት ፋርማሲዩቲካልስ ማኑፋክቸሪንግ፣ እስከ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የማስፋፊያ ፋብሪካ እቅድ ይዟል።
አሁን የፋርማሲስት ሄኖክ ተካ ሕልም መሬት ነክቶ ለምርት እያኮበኮበ ነው።
«እድሜ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፋይናንስ አቅርቦት፣ጠንካራ የክትትል እና ቁጥጥር ስርዓት!» የሚለው ሄኖክ፣ ከባልደረቦቹ ጋር ከሀገሩ ያገኘውን እውቀትና ሀብት በላቀ ኢንቨስትመንት ለሀገሩ መመለስ ስለመቻሉ ይናገራል።
❤5👍4👏2
August 26, 2026 2.5K 2