ውጤታማ የፕሮጀክት አስተዳደር ተመልክተናል - አቶ ጌታቸው
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፖሊሲ መሠረት ያላቸውን ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች ፋይናንስ ሲያደርግ ምዕተ ዓመት ተሻግሯል።
ባንኩ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የሚያበድረውን ግዙፍ ፋይናንስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት ጥብቅ የግምገማ ሥርዓቱ ተጠቃሽ ነው።
ባለፈው ሳምንትም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተገነቡ ያሉ ሦስት ግዙፍ ፋብሪካዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ያለቀለትን ኤምዲኤፍ (MDF) በገፍ የሚያመርተው «ስቲሊ ዲቢ ማኑፋክቸሪንግ» ደግሞ አንደኛው ነበር።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኮርፖሬት ደንበኞች ግንኙነት ማኔጅመንትምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በላይ እንደተናገሩት፤ የፋብሪካው የፕሮጀክት አስተዳደር በጥሩ መንገድ እየተመራ ነው።
ፋብሪካው የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃን በመጠቀም ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ ግብዓት የሚያመርት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ከግዝፈቱ አንጻር የግንባታ ሂደቱ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
ልማት ባንክ መሰል የገበያ ክፍተት የሚሞሉና የውጭ ምንዛሬ የሚያድኑ ፕሮጀክቶችን ያበረታታል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ውጤታማ ይሆኑ ዘንድም ያልተቋረጠ የክትትል፣ የግምገማ እና የድጋፍ ሥራ በልማት ባንክ እየቀረብ መሆኑን አስታውሰዋል።
በ10 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለው የስቲሊ ዲቢ ማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካ፤ ዋናውን የኤምዲኤፍ ማምረቻ ሼድ ጨምሮ የአስተዳደር ሕንፃ፣ የሠራተኞች መመገቢያ ካፌቴሪያ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንዲሁም የሙያተኞች የእንግዳ ማረፊያ ሕንፃዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ግንባታው 50 ከመቶ ተጠናቋል።
የሲቪል ሥራው ተጠናቆ ወደ ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ የተሸጋገረው የፋብሪካው ግንባታ፣ ለማሽን ተከላ የሚሆን የፋውንዴሽን ሥራ እየተሠራለት ይገኛል። ፋብሪካው ከሚፈልገው ማሽን ውስጥ አንድ ሦስተኛው በግቢው ደርሷል።
በቀን 17 ሺህ፣ በዓመት ደግሞ ከ6.2 ሚሊየን በላይ ኤምዲኤፍ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው ፣ይህም በኢትዮጵያ ቀዳሚ የዘርፉ አምራች ያደርገዋል።
«የሀገሩን ሰርዶ …» እንዲሉ፤ የአካባቢውን ጥሬ ዕቃ የሚጠቀም፣ የውጭ ምንዛሬ ከማዳን አልፎ የሚያመነጭ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የገበያ ክፍተትን የሚፈታው ይህ ግዙፍ ፋብሪካ ፡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፋይናንስና ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲሁም ክትትል በቅርቡ ወደ ምርት ይገባል።
#DBE #mdf #manufacturing
7
3August 24, 2026 2.6K