አዒሻ ቢንት አቡበክር ክፍል ስድስት ከነቢዩ ሕልፈት በኋላ ዓኢሻ ለ50 ዓመታት ያህል ኖራለች ። የትዳር ዘመኗ አሥር ዓመታት ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህ ጊዜያቶች አብዛኛውን ያሳለፈችው የአላህ መመሪያ የሆኑትን ሁለት ታላላቅ የዕውቀት ምንጮች ቁርኣንና ሱናን በማጥናት ነበር ። ዓኢሻ ቁርኣንን በልባቸው ከቋጠሩት ሦስት የነቢዩ ሚስቶች አንዷ ነበረች ። ሁለቱ ሀፍሷ እና ኡሙ ሰላማ ነበሩ ። ሀፍሷ እና ዓኢሻ ነቢዩ ካለፉ በኋላ የተከተበ የቁርኣን ቅጅ ነበራቸው ። ሐዲስ ወይንም የነቢዩን ንግግር በተመለከተ ዓኢሻ ከ 2000 ሐዲሶች በላይ ካስተላለፉልን አራት አንጋፋ ሶሃባዎች ( አቡ ሑረይራ ፣ አብዱላህ ኢብን ዑመር ፣ አነስ ኢብን ማሊክ ) መካከል ትመደባለች ። ካስተላለፈቻቸው ሐዲሶች አብዛኞቹ በቀረቤታው እንደርሷ ያለ ግለሰብ ብቻ ሊማራቸው የሚችል የነቢዩን ውስጣዊ ባህሪ የሚገልፁ ነበሩ ። ከሁሉም በላይ ግሩም የሚያሰኘው የሐዲስ እውቀቷን ያስተላለፈችልን በጹሑፍ ጭምር መሆኑ ነው ። ይህ ጹሑፍ የተዘጋጀው ከሦስት ሰዎች ባላነሱ ሲሆን ከነርሱም ውስጥ ከአስሀቦች ትውልድ በኋላ የተደነቀ ሊቅ ለመሆን የበቃው የእህቷ ልጅ ኡርዋ ይገኝበታል ። አብዛኞቹ የነቢዩ ምሁር አስሀባዎች ከአዒሻ ብዙ ዕውቀት ገብይተዋል ።አንድ ወቅት አቡ ሙሳ አል - አሽዓሪ « እኛ የአላህ መልዕክተኛ አስሀባዎች በአንድ ነገር ላይ ችግር ሲገጥመን አዒሻን ስለጉዳዩ እንጠይቃት ነበር ። » ሲሉ ተናግረዋል ። ዓኢሻ ( ረ.ዐ ) ዕውቀት የነበራት በፊቂህ ብቻ እንዳልነበር ኡርዋ ይገልፃል ።ይልቁንም በህክምና ጥበብና በሥነ ግጥምም የተካነች ነበረች ። አብዛኞቹ የነቢዩ ቀደምት አስሀባዎች በጣም የበሰለ የቀመር ( የሒሳብ ) ጭንቅላት የሚጠይቀውን የውርስ ሕግጋት በተመለከተ ምክር ትሰጣቸው ዘንድ ለመጠየቅ ወደርሷ ዘንድ ይመጡ ነበር ። ምሁራን ከቀደምቶቹ የኢስላም ፉቃሀ ( የፊቂህ ምሁራን ) ዐሙር ኢብን አል ኸጧብ ፣ ዓሊና አብዱላህ ኢብን አባስን ከመሳሰሉት ጋር ይመድቧታል ። ነቢዩ ( ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ) ጥልቅ የሆነ የኢስላም ዕውቀቷን በተመለከተ ሲጠቁሙ « የዲናችሁን ጉዳይ በተመለከተ ከዚህች መልከ ቀይ ወይዘሮ ተማሩ ። » ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል ። ዓኢሻ ( ረ.ዐ ) የጋን መብራት አልነበረችም ። ዕውቀቷን ለሌሎች በማስተላለፍና ማህበራዊ መሻሻሎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክታለች ። በምታስተምርበት ጊዜ ልብን የሚስብና ግልፅ የሆነ የንግግር ለዛ ነበራት ። የንግግር ኃይሏ በንፅፅር ሁኔታ አል አህናፋ በተባለ ሰው እንደሚከተለው ተገልጿል : - « የአቡበከርንም ሆነ የዑመርን ንግግሮች አድምጫለሁ ። የዑስማ ንን ፣ የዓሊን ፣ እንዲሁም እስካለሁበት ጊዜ ድረስ ያሉ ተተኪዎችን እንደዚሁ ። ነገር ግን በእውነቱ ከዓኢሻ አፍ እንደሰማሁት ያለ እጅግ የሚማርክና በጣም የተዋበ ንግግር ከማንም አልሰማሁም ። » ዕውቀት ለመገብየት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ድንበር አቋርጠው ይመጣሉ ። የሴቶቹ ቁጥርም ከወንዶቹ እንደሚበልጥ ይነገራል።ለሚቀርብላት ጥያቄ መልስ ከመስጠቷ በተጨማሪ በጥበቃዋ ሥር በርሷ መመሪያ መሠረት የምታስጠናቸው የቲም የሆኑ ልጆችና ልጃገረዶች ነበሯት ። እነርሱም ከርሷ መመሪያ ከሚቀበሉት ዘመዶቿ ተጨማሪ ናቸው ። ከዚህም የተነሳ ቤቷ ት / ቤት ነበር ለማለት ይቻላል ። የተወሰኑ ተማሪዎች ከሁሉ የመጠቁ ነበሩ ። የእህቷ ልጅ ኡርዋ ( ረ.ዐ ) የተደነቀ ሐዲስ ዘጋቢ እንደነበር ቀደም ሲል ጠቅሰናል ። ከሴት ተማሪዎቿም ዑምራ ቢንት አብዱረህማን ( ረ.ዐ ) ሳትጠቀስ አታልፍም።ምሁራን ይህች ሴት ( ዑምራ ) ታማኝ ሐዲስ አስተላላፊ እንደነበረችና የአዒሻ ጸሐፊም በመሆን የሚጻፍላትን ደብዳቤ በመቀበልና ምላሽ በመስጠት ታገለግል እንደነበር ይናገራሉ ። አዒሻ ( ረ.ዐ ) ትምህርት እንዲስፋፋ በተለይ ሙስሊም ሴቶች የሸሪዓን ህግ እንዲያውቁና ጥልቅ የኢስላም ግንዛቤ እንዲኖራቸው ታደርግ የነበረው ጥረት በምሳሌነት የሚጠቀስና ሊከተሉት የሚገባ ተግባር ነው ። ✍ ሙሐመድ ኢብን ፈድሉ 【 📚ሃያቱ ሶሃባ 】 “ ኢንሻ አላህ ይቀጥላል ” ¤ t.me/Darutewhide/2852
8