አዒሻ ቢንት አቡበክር ክፍል አምስት በነቢዩ የሕይወት ዘመንም ሆነ ከህልፈታቸው በኋላ ከዚሁ ምርጫዋ ዝንፍ… — DARU-TEWHID [ዳሩ-ተውሒድ] — TG.ME

አዒሻ ቢንት አቡበክር ክፍል አምስት በነቢዩ የሕይወት ዘመንም ሆነ ከህልፈታቸው በኋላ ከዚሁ ምርጫዋ ዝንፍ አላለችም። የኋላ ኋላ ሙስሊሞች በኃብት በተትረፈረፉበት ጊዜ በአንድ ወቅት የአንድ መቶ ሺህ ዲርሀም ስጦታ አግኝታ ነበር ። ገንዘቡን በምትቀበልበት ጊዜ በጾም ላይ ነበረች ።ታዲያ የተቀበለችውን ገንዘብ ካዝና ውስጥ አላስገባችውም ።ይልቁንም በቤቷ አንዳች ነገር ባይኖራትም ምንም ሳታስቀር ሁሉንም ገንዘብ ለድሆችና ምፅዋት ለሚያሻቸው አከፋፈለች ።ይህን ካደረገች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የቤት አገልጋይዋ « የምታፈጥሪበት ( ጾምሽን የምትፈችበት ) የአንድ ዲርሀም ሥጋ ልትገዢ ትችያለሽን ? » ስትል ጠየቀቻት ። « ባልረሳው ኖሮ ለእርሱ የሚሆን ዲርሃም እንኳ ይኖረኝ ነበር » ስትል መልሳላታለች ። ነቢዩ ህመም በጠናባቸው ጊዜ ሁሉም ሚስቶቻቸው ባቀረቡት ሐሣብ መሠረት በአዒሻህ ቤት ነበር የተስታመሙት ። ለብዙ ጊዜም ራሳቸውን ከደረቷ ወይንም ከጭኗ ላይ በማሳረፍ በአልጋቸው ላይ ይተኛሉ ። ከወንድሟ የጥርስ መፋቂያ ( ሲዋክ ) በመውሰድ እንዲለሰልስላቸው በጥርሷ አኝካ ለነቢዩ ሰጠቻቸው ። ምንም እንኳን አቅም ቢያንሳቸው በሲዋኩ ጥርሳቸውን አሳምረው ፋቁት ። ብዙም ሳይቆዩ ሕሊናቸውን እየሳቱ መጡ ። አዒሻም የሞት ደጃፍ መከፈቱን ተረዳች ። ከተወሰነ ቆይታ በኋላም አይናቸውን ከፈቱ ። አዒሻም ነቢዩ ዓይናቸውን እንደገና በከፈቱ ጊዜ አትኩራ እያየቻቸው « አንድም ነቢይ በጀነት ያለውን ቦታ ሳያይ እንዲሁም የመሞት ወይም በአዱንያ የመቆየት ምርጫ ሳይሰጠው ሞት አትቀድመውም ። » ሲሉ ተሰሙ ። « አዎ ! ከእንግዲህ እኛን አይመርጡም » ስትል ለራሷ ተናገረች ። በዚህን ጊዜም « በጀነት ከሚገኘው ከታላቁ ማኅበረሰብ ጋር ፥ ከነዚያ አላህ የቸርነቱን ፀጋ ካዘነበላቸው ጋር ፣ ከነቢያቶች ፣ ከሹሀዳዎቹ ( ከሰማዕታት ) እና ቀጥተኛን መንገድ ከተመሩት … » የሚል ድምፅ ሰማች ። እንደገናም « ጌታዬ ሆይ ! ከታላላቁ ማህበረሰብ ጋር » የሚል የለሆሳስ ድምፅ ሰማች ለመጨረሻ ጊዜ።ደረቷን ተንተርሶት የነበረው ራሳቸው ቀስ በቀስ እየከበዳት መጣ ። በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሶሃባዎችም ማልቀስ ጀመሩ ።ዓኢሻም የነቢዩን ራስ ትራስ ላይ በማስደገፍ ከሀዘንተኞቹ ጋር ተቀላቀለች።ከተኙበት አልጋ አጠገብ የቀብር ጉድጓድ ተቆፈረ ።ከዚያም የመጨረሻው ነቢይ በታላቅ ሀዘን ተቀበሩ። ✍ ሙሐመድ ኢብን ፈድሉ     【 📚ሃያቱ ሶሃባ 】       “ ኢንሻ አላህ ይቀጥላል ”       ¤ t.me/Darutewhide/2852

👍13
August 1, 2026 1.6K 4 6