አዒሻ ቢንት አቡበክር ክፍል ሶስት ነቢዩ በመዲና ሳሉ ከሚስቶቻቸው ሁሉ አዒሻን ይበልጥ ይወዱ እንደነበር ግልፅ ነው።አንዳንድ ባልደረባዎቻቸው አዘውትረው « የአላህ ልዑክ ሆይ ! በዓለም ላይ እጅግ በጣም የሚወዱት ማንን ነው ? » ሲሉ ይጠይቋቸው ነበር ። ለዚህም ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ እንደ ጥያቄው ባህሪ የሚለያይ ነበር ። ለሴት ልጆቻቸውና ለነርሱም ልጆች ፥ ሌላ ጊዜ ለአቡበክር ፥ ለዓሊ ፣ ለዘይድና ለልጁ ለኡሳማ ) ውዴታ እንዳላቸው አሳውቀዋል ። ነገር ግን ከሚስቶቻቸው መሃል ከኸዲጃ ቀጥሎ ማንን ይበልጥ እንደሚወዱ ሲጠየቁ ምላሻቸው « አዒሻ ናት » የሚል ነበር ። እርሷም እጅግ አድርጋ ትወዳቸዋለች ። ዘወትር ውዴታቸውን የሚያረጋግጥላት ነገርም ከእርሳቸው ትፈልጋለች ። አንድ ወቅት « ለኔ ያለህ ፍቅር እንዴት ነው ? » ስትል ጠይቃቸው « እንደ ቋጠሮ ሲሉ መለሱላት ። ትርጓሜውም እንደብረት የጠነከረና በቀላሉ የማይፈታ ማለት ነው ። ለነብዩ ያላት ፍቅር ቅናት የታከለበት ስለነበር ከርሷ የበለጠ ትኩረት ለሌሎች ሚስቶቻቸው እንዲሰጡ አትፈቅድም ነበር ። ከዚህም የተነሳ « የአላህ ልዑክ ሆይ ! እባክዎን ይንገሩኝ ! ለመሆኑ በሁለት ሸለቆዎች መሃከል ቢሆኑና አንዱ ሸለቆ የተጋጠ ሌለኛው ልምላሜው ያማረ ጨፌ ቢኖረው በየትኛው ላይ ከብቶችዎን ሊያሰማሩ ይሻሉ ? » ስትል ጠየቀቻቸው።ነቢዩም « ባልተጋጠጠው ሸለቆ ላይ » ሲሉ መለሱላት ። አዒሻም « ታዲያ እኔኮ እንደሌሎቹ ሚስቶችዎ አይደለሁም ። ምክንያቱም ሁሉም ቢሆኑ ሌላ ባል አግብተው የነበሩ ናቸው ። » በማለት የርሷን ማንነት ልታስታውስ ትሞክራለች ። በዚህን ጊዜም ነቢዩ ድርበብ የተላበሰ ፈገግታቸውን በማሳየት ዝም ይላሉ ። አዒሻ በኸዲጃ በጣም ትቀና ነበር ። አዒሻ እንዲህ ትላለች : - « ዘወትር ስሟን ስለሚጠሩ ፣ እንዲሁም ከከበረ ድንጋይ የተገነባ ቤት በጀነት እንደተዘጋጀላት ብሥራት ይነግሩ ዘንድ ከአላህ በመታዘዛቸው ፥ በኸዲጃ ( ረ.ዐ ) እንደቀናሁት በማናቸውም የነቢዩ ሚስቶች አልቀናሁም ። በግ ባረዱ ቁጥር የሥጋውን የተወሰነ ክፍል የልብ ወዳጆቿ ለነበሩ ይልካሉ ። በዚህም ምክንያት ‹ በርስዎ ቤት ከኸዲጃ በስተቀር ሌላ ሴት በዓለም ላይ የለም › እያልኩ አዘውትሬ እነግራቸው ነበር ። » ✍ ሙሐመድ ኢብኑ ፈድሉ 【 📚ሃያቱ ሶሃባ 】 “ ኢንሻ አላህ ይቀጥላል ” ¤ t.me/Darutewhide/2852
12
2