አዒሻ ቢንት አቡበክር ክፍል ሁለት የነቢዩ ሚስት የሆነችው የ 10 ዓመት ልጅ ሳለች በመካ ሲሆን ፥ እስከ ሁለተኛው ዓመተ – ሂጅራና በግምት የ 14 ና የ 15 ዓመት ወጣት እስከሆነችበት ጊዜ ድረስ ሰርጓ አልተከናወነም ። የሰርጓን ስነ ሥርዓት በተመለከተ እንዲህ ስትል ተርካልናለች : - « አንድ ቀን እየተጫወትኩ ነበር ። ረጅሙና ዘንፋላው ፀጉሬ በወጉ አልተጐነጐነም ። ቤተሰቦቼ ከምጫወትበት ቦታ መጥተው ወደቤት በመውሰድ ለሰርግ እንድዘጋጅ አደረጉኝ ። በባህሬይን የተሠራ ቀይ ሰረዝ ያለው የሙሽራ ልብስ አለበሱኝ ። እናቴም ጥቂት የመዲና ሴቶች ከበር ላይ ቆመው ወደሚጠብቁባት አዲሱ ጐጆዬ ወሰደችኝ ። ( ጋብቻሽ ለመልካምና ለደስታ ይበለው ! ሁሉም ያማረ ይሁንልሽ › ሲሉም በደስታ ተቀበሉኝ ። ከዚያም በፈገግታ የተሞሉት ነቢይ በተገኙበት የዋንጫ ወተት ቀረበ ። ነቢዩ ( ሶ.ዐ.ወ ) ከወተቱ ተጐንጭተው ሰጡኝ ። እኔም ስላፈርኩኝ በእጄ እንደያዝኩት ቀረሁ ። ቢሆንም እንድጠጣ ስላደፋፈሩኝ ጠጣሁ ። ቀሪውን ከአጠገቤ ተቀምጣ ለነበረችው እህቴ– ለአስማ– አሳለፍኩ ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሁሉም እየተቀባበሉ ተጐነጩለት ። በዚህ እጅግ ቀላልና የተባረከ በሆነ መልክ ነበር የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው ። ” የነቢዩ ሚስት መሆኗ የጨዋታ ሕይወቷን አልገታውም ። ወጣት ጓደኞቿ ከቤት ሊጐበኟት አዘውትረው ይመጡ ነበር ። ስለዚህም ሁኔታ እንዲህ ስትል ተናግራለች : - « ጓደኞቼ ከሆኑ ልጃገረዶች ጋር በመጫወት ላይ ሳለሁ ነቢዩ በሚገቡበት ጊዜ ጓደኞቼ ቤቱን ለቀው ይወጣሉ ። ነቢዩም የእነርሱ ከኔ ጋር መሆን እንደሚያስደስተኝ ስለሚያውቁ ለኔ ውዴታ ሲሉ እንዲመለሱ ያደርጓቸዋል ። አንዳንድ ጊዜም ቤቱን ከመልቀቃቸው በፊት ‹ ባላችሁበት ሁኑ › በማለት ያረጓጓቸዋል ። እንዲያም ሲል በጨዋታቸው ላይ ይሳተፋሉ ። » የአዒሻ የመጀመሪያው የመዲና ሕይወቷ ትጋትና ጥንካሬን የሚጠይቅ ፈታኝ አጋጣሚ ነበር ። በአንድ ወቅት አባቷና ከርሱ ዘንድ ያረፉ ሁለት አስሃባዎች በመዲና በተወሰኑ ወቅቶች የተለመደ በሆነ አደገኛ ትኩሳት ታመሙ ። በዚያን ጊዜ አዒሻ አንድ ጠዋት አባቷን ለመጐብኘት እንደሄደች ሦስቱም በሽተኞች ተዳክመውና ሰውነታቸው ሟሾ ስላገኘቻቸው ከባድ ድንጋጤና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አደረባት ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አባቷ ምን እንደሚሰማቸው ስትጠይቅ ፥ ትርጓሜው ባልገባት የቁርኣን ምዕራፍ መለሱላት ። በሁኔታው እጅግ ተረብሻ ወደቤቷ በመመለስ ለነቢዩ ፥ « በሽታው ስለጠናባቸው ይቃዣሉ ። » አለቻቸው።ነቢዩም ምን ምን እንዳሉ ጠየቋት ። ምንም እንኳ ትርጓሜው ባይገባትም የሰማችውን ንግግር ቃል በቃል ነገረቻቸው።ከንግግሯም ነቢዩ የበሽተኞቹን ሁኔታ ለመረዳት ቻሉ።ይህ ገጠመኝ እጅግ አስደናቂ የሆነውን የማስታወስ ችሎታዋን ያሳየናል ።ይህም ችሎታዋ ጊዜ እየገፋ በሄደ ቁጥር በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ የነቢዩን ንግግሮች እንድታከማች አግዟታል ። ✍ ሙሐመድ ኢብን ፈድሉ 【 📚ሃያቱ ሶሃባ 】 “ ኢንሻ አላህ ይቀጥላል ” ¤ t.me/Darutewhide/2852
15