Book for all Ethiopia: post #506 — TG.ME

ሺ ሰማኒያ [1080]

አንድ ቅዳሜ ቀን ጫማዬን ለማስጠረግ የሆነ ቦታ ቆሜ ሳለሁ አንድ መበለት እኔ ወዳለሁበት መጥተው ስባሪ ሣንቲም እንድጥልላቸው እጃቸውን ዘረጉልኝ፡፡

"ይቅርታዎትን? እዛች ቤት ይግቡና ቁርስ ይዘዙ፤ አብረን እንበላለን" አልኳቸው፡፡

እጃቸውን አየር ላይ እንደዘረጉ ዝም ብለው አዩኝ፡፡

"ጫማዬን አስጠርጌ እስክጨርስ የሚፈልጉትን አዘው ይጠብቁኝ" አልኳቸው፡፡

"ኧረ ብሩ ይበቃኛል" አሉ የሆነ አይነት ሳቅ እና መሽኮርመም እያሳዩኝ፡፡

ብሩን ብቻ የፈለጉ አይመስልም፡፡ ሳይጠራጠሩ፤ ምናልባት እረስቶት ባይመጣ ብለው የፈሩ ይመስለኛል፡፡

ለመሄድ ከተስማሙ በኋላ ዘወር እያሉ አንድ ሁለት ጊዜ ተመለከቱኝ፡፡

"ይቅርታ ትንሽ አፍጥንልኝ" አልኩ ጎንበስ ብዬ፡፡

ቀይር ብሎ ቆርቆረውን ከመምታቱ በፊት ጫማዬን ለመቀየር እግሬን ወደ ላይ ብድግ አደረግሁለት፡፡

"እሺ" አለና ቆርቆሮውን ኳ! አደረገው፡፡

ቁርስ የምበላበት ቤት እንደገባሁ ወደዚህ የላኳቸውን እናት በዐይኔ ፈለኳቸው፡፡ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን ጥቁር ፌስታል ጭናቸው ላይ እንዳደረጉ በሩ አጠገብ ጭብጭ ብለው አየኋቸው፡፡

"ለምን ይሸከማሉ?" አንደኛውን ወንበር ወደእሳቸው ሳብ አደረኩና፤

"እዚህ ላይ ማስቀመጥ ይችላሉ" አልኳቸው፡፡

እቃውን እስቀምጠው ወደኔ ለማየት እንዲመቻቸው ትንሽ ዘወር አሉ፡፡

"ምን አዘዙ?"

"ምንም" አንገታቸውን አቀረቀሩ፡፡

"እሺ፡፡ . . . ፍርፍር ነገር ይሁን ወይንስ ቂጣ ነገር? ጨጨብሳ፣ ቅንጬም ከፈለጉ አለ"

"ቅንጬ ይሸጣል?" ገረማቸው፡፡

"አዎ አለ" አሁንም ትንሽ ተሽኮረመሙ፡፡

"ቅንጬ ይሁንለዎት?"

"እሺ!"

አስቸናጋጁን ጠርቼ ቅንጬ እና ጨጨብሳ እንዲያመጣልን ነገርኩት፡፡

"የፈጠነ! አንድ ሌላ ጨጨብሳ እና አንድ ቅንጬ" አለ አስተናጋጁ ድምጹን ከፍ አድርጎ፡፡ ከንግግሩ ጋር አብሮ የተበላባቸውን እቃዎች ለማንሳት ወደጠረጴዛዎቹ ይበራል፡፡

ምን ብዬ ወሬ እንደምጀምር ስለጠፋብኝ፡፡

"ልጅ አለዎት?" በጊዜው የመጣልኝን ጥያቄ አቀረብኩ፡፡

"የለኝም"

ጎንበስ ብለው ያደፈ ነጠላቸውን ማፍተልተል ያዙ፡፡

የማይሆን ርዕስ የመረጥኩ ስለመሰለኝ ቀጥዬ የምጠይቀው ነገር ሁሉ ነውር ሆነብኝ፡፡

"የሚጠጣ ምን ይምጣላችሁ?" አለ አስተናጋጁ አጠገባችን ቆሞ ቁልቁል እያየን፡፡

"ማዘር! የሚጠጣ ምን ይፈልጋሉ?"

"ምንም አልፈልግ፡፡ በልቼ ስጨርስ ቡና ልጠጣና አንድኛዬን በደንብ አድርጌ ልመርቅህ?" ንግግራቸው ውስጥ "እሺ በለኝ?" የሚል ልመና ነበረው፡፡

"አሺ፡፡ . . . ትንሽ ቆይተን ትኩስ ነገር እንጣለን" አልኩኝ፡፡ መጀመሪያ እሳቸውን ቀጥዬ እሱን እየተመለከትኩ፡፡

ወይዘሮ መብራት ርዕሶም ይባላሉ፡፡ ዕድሜአቸው ሰባዎቹ ውስጥ ይገመታል፡፡ ተወልደው ያደጉት ከአሥመራ ወጣ ብላ ያለች ትንሽ መንደር ውስጥ ነው፡፡

በቀይ ኮከብ ዘመቻ አስመራ ያለ አንድ ቡና ቤት ውስጥ ጽዳት ሠራተኛ ሆነው ይሠሩ ነበሩ፡፡ ቤቱ ብዙ የደርግ ወታደሮች ከሚያዘወትሩት እንደነበር በታሪክ ጭምር ይታወቃል፡፡

***
ልክ እንደዛሬው ቅዳሜ እረፋድ ላይ፤ ቤቱን አጽድቼ ቁርሴን ልበላ ቀጭ እንዳልኩ፤ አንድ የደርግ ወታደር በሩን ከፍቶ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ጥግ ላይ ሁለት መኮንኖችን ስለነበሩ ትንሽ ደንገጥ አለ፡፡ ለእነሱ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ እጄን ይዞ ወደ ጓዳ ወሰደኝ፡፡
*
አስተናጋጁ አንድ የጀበና ቡና እና አንድ ሻይ ይዞልን መጣ፡፡
*
ወደ ውስጥ እንደገባን፤

"ሻለቃ ባሕሩ ተመቶ ሆስፒታል ገብቷል" አለኝ፡፡

"*ብህይወት አሎ ድዩ ሞይቱ?" አልኩት፡፡

"ደህና ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ሊሄድ ስለሆነ ሊያገኝሽ ይፈልጋል" አለኝ፡፡ ተያይዘን አሥመራ ሆስፒታል ሄድን፡፡

የሚታከምበት ክፍል ስገባ፤ ገና በር ላይ እንዳለሁ አልጋው ላይ ቁጭ ብሎ አየሁት፡፡ በጣም ደስ አለኝ፡፡ እቅፍ አድርጎ ሳመኝና አልጋው ጠርዝ ላይ አስቀምጦ፡፡

"ቦርድ የምወጣ ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ አብረን እንሂድ?" አለኝ፡፡

"አዲስ አበባ?!" በጣም ደነገጥኩ፡፡ እሱ ግን ፈገግ እያለ፤

"ከዚህ በኋላ ሚስቴ አድርጌሻለሁ" አለኝ፡፡

*
"አሁን እዚህ ያገኘኸኝ ለምን ይመስልሃል? ታናሽ እኅቴን ይዤ ከእሱ ጋር አዲስ አበባ መጣሁ "

*
ትንሽ ፈገግ ማለት ስጀምር ፊታቸው ጭፍግግ ሲል አየሁት፡፡ የህይወታቸው አሳዛኝ ክፍል ሊጀምር እንደሆነ ስለገባኝ ትንሽ ሰብሰብ ለማለት ሞከርኩ፡፡

"*ዕድል ወድ ሰብ ይገርምዩ" አሉ ጨርሰው ያስቀመጡትን ስኒ እንደገና ፉት እያሉ፡፡

"ይደግማሉ?" አልኳቸው፡፡ በጭንቅላታቸው ብቻ መለሱልኝ፡፡

***
አዲስ አበባ መኖር ከጀመሩ ሠላሳ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ባለቤታቸው ከዛሬ አሥራ ሁለት ዓመት በፊት ሲሞቱ ያስቀመጡላቸው ምንም አይነት ጥሪት አልነበረም፡፡ ይባስ ብሎ ይኖሩበት የነበረው ቤት ከባለቤታቸው ወንድም ጋር የፍርድ ቤት ክርክር ገጠመው፡፡

*
ይረዳኛል ብዬ ስላሰብኩ ለባለቤቴ ጓደኛ ነገሩን በዝርዝር አጫወትኩት፡፡ የጠበቃ ብር እንዳይበዛብኝ የቤቱን ዋጋ ዝቅ አድርገሽ ተከራከሪ ብሎ ነገረኝ፡፡ ሰውየው ከባለቤቴ በላይ የወንድምዬው ወዳጅ ነበር፡፡ ተንኮል እንደነገረኝ የገባኝ ነገሩ ካለፈ በኋላ፣ ቆይቶ ነው፡፡ ወንድምዬው ይህንን መሠረት አድርጎ፤ ለዳኞቹ ጉቦ ሰጠና የተባለውን ብር ለእኔ ከፍሎ ቤቱን እንድለቅ ለፍርድ ቤቱ አመለከተ፡፡

*
ትኩሱን ቡና ከሦስት ጊዜ በላይ ፉት አላሉትም፡፡

*
ብሩን ወስጄ ቤቱን እንድለቅ ተፈረደ፡፡ ቤቱ ግን ሚሊዮን ያወጣ ነበር፡፡ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ብር እና የታመመች እኅቴን ይዤ ከቤት ወጣሁ፡፡ ሦስት ዓመት በትክክል መኖራችንን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለህክምና፣ ለኑሮ እያልን ብሩን ጨረስነው፡፡

ለረጅም ጊዜ ዝም ብለው መሬት መሬቱን ሲመለከቱ ቆይተው፤

"*ስለምንታይ አብዚ ዝረከብካኒ ይመስለካ?" አሉኝ፡፡ ዝም አልኳቸው፤

"ልመና ወጣን፡፡ አሁን እስጢፋኖስ በተክርስቲያን የላስቲክ ቤት ሠርተን ነው የምንኖረው"

የማይሠራ የሬድዮ ድምጽና የተበላሸ የቴሌቪዥን ምስል፤ መስማትና ማየት ጀመርኩ፡፡

***
-----------------------------------------
* ብህይወት አሎ ድዩ ሞይቱ? - በህይወት አለ ወይንስ ሞቷል?

* ዕድል ወድ ሰብ ይገርምዩ - የሰው ልጅ ዕድል በጣም ይገርማል፡፡
April 3, 2022 11K 13