ጥሪ_ወደ_ሞት ፡ ፡ #ክፋል_ስምንት ፡ ፡ #በአህመድ_ሁስ(ሻድ) ፧፧ የዕይታ አድማሴን ለማጥበብ ስል እጆቼን… — አትሮኖስ — TG.ME

#ጥሪ_ወደ_ሞት ፡ ፡ #ክፋል_ስምንት ፡ ፡ #በአህመድ_ሁስ(ሻድ) ፧፧ የዕይታ አድማሴን ለማጥበብ ስል እጆቼን ዓይኔን ሳልጨፍን ከፊቴ ላይ አስቀምጣለሁ። የእጆቼን መዳፍ ድረስ በማየት ብቻ ዕይታዬ ውስጥ የሰው ልጆች እንዳይገቡብኝ እጥራለሁ። የሰው ልጆችን እጠላለሁ። ፍቅር ይሉት ነገር ልቤን ጎብኝቶኝ አያውቅም:: ስለመኖሩም እጠራጠራለሁ። ልቤ ደም ሲረጭ ብቻ ነው የኖረው። የሰው ልጆች የውስጣቸውን ምናብ በገሀዱ ሊያገኙት የመፈለጋቸው ውጤት ነው ፍቅር። አዕምሯችን ውስጥ በምናብ የተሳለው የሌሎች መልክና ቁመና ባህሪና ስብዕና በምድር ላይ በአንዱ ስጋ ላይ ሲገለጥ ፍቅር ያዘን እንላለን። ያፈቀርነው ቀድመን በአዕምሯችን ስስስስያስቀመጥነውን ማንነት እንጂ አዲስ ያገኘነውን እንግዳ አይደለም። እኔ በውስጤ ስዬ ያስቀመጥኩት ምናባዊ አቋምና ስብዕና ባለመኖሩ ፍቅርን አላውቀውም። በዘመኔ የሰው ልጆች እንጂ ሰዎች ስለሌሉ ይህን ስያሜ አልጠቀመውም። ሰዎች በተፈጥሯቸው ገደልና ሜዳውን የሚለዩ ሞራል የተቸራቸው ህሊናቸው ዘወትር ሰለሚመረምራቸው እጅግ የተለዩ ፍጡራን ናቸው። እነዚህ የተፈጥሮ ሁሉ ገዢዎች ዛሬ ዛሬ ላይ ከትውልዴ መዝገብ ላይ ተፍቀዋል። እንደአጋጣሚ ቢገኙ ድንቅ ፍጥረቶች ሆነው ይጎበኛሉ። ዓለም ስለእነሱ ጠዋት ማታ ይዘግባል። መልካምነትና ሞራላዊነት የሰው ተፈጥሮ እንዳልሆነ ሁሉ በመደነቅ ስለመልካምነታቸው ይለፈፋል። አሁን ዘመኔን የሚጋሩኝ በጠቅላላ የእነዚህ ድንቅ ፍጥረቶች የልጅ ልጆቻቸው ናቸው። ስለዚህም ነው "ሰዎች" ሳይሆን "የሰው ልጆች" እያልኩ የምጠራቸው። እነዚህን ከሌላው በተለየ መልኩ እጠላቸዋለሁ። ነፍሶቻቸው ጋለሞታ ነች። እዚህም እዚያም ትረግጣለች። አቋምና ልኳን መስፈሪያ ልክ የላቸውም። እዚያ ተራራ ላይ እንደበቀለ ወፍ ዘራሽ ዛፍ የበቀሉ ይመስላቸዋል። ማለትም በስህተት ተወልደው ያለ ምክንያት የሚኖሩት ህይወት ውስጥ ይፍገመገማሉ። መፈጠራቸው ለዓላማ መሆኑን ይዘነጋሉ። ጦርነትን ሲያዩ ሀይቅ ዳር ተቀምጠው በተፈጥሮ ራሳቸውን እያደሱ አይነት ተዝናኖት ውስጥ ይሆናሉ። ደም  የውሃ ያክል ቀላል ሆኖላቸዋል።ጥርሶቻቸውን በመሰሎቻቸው ፍጥረቶች አጥንት ይፍቃሉ። ሀብቶቻቸው ባልተገቡ መንገዶች የመጡ ናቸው። ኡፍ ጉዳያቸው! ከእነሱ ጋር ህብረት የለኝም። ራሴን ችዬ በራሴው ጎዳና ላይ የምጓዝ ብቸኛ የሰው ልጅ ነኝ። ጥርሶቼን በምላሴ ጫፍ ዳበስኳቸው ይሻክራሉ። የአፌ ጥጋ ጥግ አልጌ የወረረው ይመስል ምላሴን ይኮሰኩሰኛል። የአፌ ጠረን አሳስቦኝ ለማፅዳት ሞክሬ አላውቅም። ማንም አጠገቤ ሆኖ ለማያሸተው የአፌ ጠረን ለምን ስል ጉልበት ላባክን። የጥርስና የአዕምሮ ሁኔታ ተመሳሳይ ይመስለኛል።ሁለቱም ካልተንቀሳቀሱና   የሚያላምጡት ሀሳብና ምግብ ካልሰጠናቸው ይቀየራሉ። ለአዕምሯችን የሀሳብን ለጥርሳችን ደግሞ የምግብን ግብዓት ካላገኙ ለዙሪያችን ይሰነፍጣሉ። ዕድሜዬ ግን ስንት ሆነ? አስር? ሀያ አምስት? ወይስ ሰማኒያ ዓመት ሞላኝ ይሆን? አላውቅም! ቀን የመቁጠር ቅንጦትን መኖሬ አይሻም። ምናልባትም አንድ የሚባል የዕድሜ አቆጣጠር ካለ በሱ ብጠራው የተሻለ ይሆናል። ዛሬዬና ነገዬ መካከል ምንም ልዩነት የሌለኝ እኔ ሀምሳና ሰባ ዓመት ብዬ ራሴን የቁጥር ሸክም አልጭንበትም። አንድን ዓመት ምናልባትም ለመቶ ያህል ዙር ደጋግሜ ኖሬያት ይሆናል። የተወለድኩበትን ቀንና ዓመት አላውቅም። ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ ጉቶ እግሮቼን ስጎትት ነው ራሴን ያገኘሁት። ድባቴያም ህይወቴን ሳባብል ነው ከዓለም ጋር የተዋወቅኩት። የሰው ልጅ ልክ በምጣዱ ላይ እንደሚዞረው የእንጀራ ሊጥ ነው። ከሰፊው ክብ ይጀምርና እየዞረ ክቡን እየገጠመ መጥቶ መሀል ላይ ይዘጋል። የሚጀምርበት ነጥብ አይታወቅም። በዚህ በኩል ነው ብለን አቅጣጫ አናስቀምጥለትም። የሊጡ ፍፃሜው ግን መሀል ላይ መሆኑ ግልፅ ነው። ሰፊው ክብ ተሰብስቦ መሀል ላይ ሲገጥም እንዲበስል ይገጠማል። የሰው ልጅም እንዲሁ ነው። የሚወለደው ራሱን በቅጡ ከማያውቅበት ከነፃው ዓለም ነው። ነፃነቱ ልክ እንደሰፊው ክብ ነበር። ራሱን እያወቀ እየተማረ እየተመራመረ ብሎም እየኖረ ሲመጣ ክቡን እያጠበበ ይመጣል። እየኖረ በመጣ ቁጥር የሚጠብ ክብነት ተሰጥቶታል። ልክ መሀሉ ላይ ሲደርስ ፍፃሜውን ያገኛል። በምድር ላይያለው ቆይታ ተጠናቀቀ። በሞት! ሁለቱም ከዚህ ወዲያ ይከደናሉ። የሰው ልጅ ግብዓተ መሬቱ የምጣዱ ላይ ሊጥ ደግሞ በክዳኑ ይዘጋሉ። ከዚህ ኋላ ሁለቱም ወደ ቀጣዩ ከፍታቸው ይንደረደራሉ። ምጣዱ ሲከፈት የፈሰሰበት ሊጥ እንጀራ ተብሎ ይወጣል። ከዚህ ወዲያ ይህ እንጀራ ነፍስ አለው። ነፍስ ያላቸውን ፍጡራኖችን ይመግባል። በእንጀራኛ ቋንቋ ብናወራው የተፈጠርኩበትን ዓላማ እየኖርኩ ስለሆነ ደስተኛ ነኝ ሊለን ይችላል። እዚህ  ደረጃ የደረሰው እንጀራ በመጀመሪያ የአፈርን ደረት ሰንጥቆ ከወጣው ጤፍ ነው። ከአፈር ወጥቶ በአፈር የተፈጠሩ የሰው ልጆችን ነፍስ ያስቀጥላል። ከአፈሩ የወጣው ጤፍ ከመታጨድ አንስቶ እስከ ወፍጮ ቤት ጉዞው የመከራ  ነው። ይህ መከራው ከሰው ልጅ የህይወት መልክ ጋር ተመሳሳይ ነው። መታጨድ… መወቃት… እያለ በስለታማ መፍጫ ውስጥ መድቀቅ። በመጨረሻም ታላቁን ስኬት መቀናጀት የግድ ይለዋል። እሱ ስኬት የሚጀምረው ከብስለቱ በኋላ የሚመጣው "መድረስ" ነው። ከምጣዱ ላይ በስሎ በሰፌድ ላይ ተነጥፎ ወጥቶ ነፍስ ያላቸውን ሲመግብ የመኖር ግቡን እያሳካ ነው። ለዚህ ክብር የበቃው ደግሞ ያቺን ክብ ዞሮ ስለገጠመ ነው። የሰው ልጅም ደስታው የሚጀምረው ከዚህች የመኖር ክብ መግጠሚያው ላይ ሲደርስ ብቻ ነው። ተወልዶ አድጎ እየኖረ በመጣ ቁጥር ክቡን ጨርሶ ሲገጥም በሞት ምድርን ይሰናበታል። ልክ እንደ እንጀራው ሁሉ ነፍሱ አገልግሎት የምትሰጠው ከሞቱ ማግስት ነው። ያኔ እውነተኛውን ደስታ ማጣጣም ይጀምራል። ለጋገረው አካል አገልግሎት የሚሰጠው ሲሞት ነው። ለዚህ ነው የሰው ልጅ በዕረፍት ውስጥ ያለውን ደስታ ማጣጣም ከፈለገ በመጀመሪያ ይሙት የምለው። ራሱን ይገላግል። እኔም ጥቂት ሰዓታት ቀርተውኛል። ከዚህ ወዲያ ብዙ የምኖር አይመስለኝም። ብዙ የህይወት መስመሮች ላይ ክብ እየሰራሁ ኖሬያለሁ። ከዕለት ወደ ዕለት ክቤን እያጠበብኩ መጥቻለሁ። ክቤ እየጠበበ መሆኑን ሳውቅ ልቤ እየፈነጠዘች መጣች። ደስታ እፍን እያደረገኝ ነው። ተጋግሬ ነፍስ ልዘራ ነው። በአፈሩ ክዳኔ ውስጥ ዓይኖቼን እከፍታለሁ። ይህን ሳስብ አንገቴን ወደላይ ቀና አድርጌ ዓይኖቼን ጨፈንኩ። ወፍራም አየር ወደ ውስጤ ሳብኩ። የምገባበት ምድር የአፈሯ ጠረን ከወዲሁ አወደኝ። ትኩስ ለም አፈር እንደሚንተከተክ የወጥ ቁሌት ድምፅ እየተሰማኝ ነው። ስጋዬን ተቀብሎ ህይወት ሊዘራብኝ እየተዘጋጀ ነው። ትከሻዬ የተነቀለ ያህል ሸክም አጣሁበት። ምድር እየጠበቀችኝ ነው። እንደ እናት እቅፏን ዘርግታ እሰይ እሰይ እያለችኝ ነው። መሮጥ አለብኝ። መፍጠን አለብኝ። የምጣዴን መሀል ዛሬ አርፍባታለሁ። አፈር በተባለ ክዳን ስር እከተታለሁ። ያኔ እበስልና ትክክለኛውን ደስታ ለዘላለሙ አጣጥማለሁ እውነተኛውን ግዙፍ ህይወት እኖራለሁ። ከማይደርቀው ለምለም ሜዳ መሀል ሆኜ እጆቼን እዘረጋለሁ፡ ከፀሀይ መውጫ በኩል በሚመጣው ነፋስ ልብሶቼን አውለበልባለሁ። እግሮቼ እርጥብ ሳር ላይ ይዘላሉ ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በሞቴ ማግስት ነው። ቢራቢሮዎች ከግንባሬ ላይ ያርፋሉ። የህፃናት የረሀብ ለቅሶ ሳይሆን የቡረቃ ሳቅ ከርቀት ይሰማኛል። በህይወት ቆሜ ያላገኘሁት ሀሴት ሞቴ ይሸልመኛል።

❤9👍1
August 25, 2026 2.7K 1