አትሮኖስ: post #95656 — TG.ME

​​ይህ ትውልድ ቃጭል ሳይሆን ሞቱን አንጠልጥሉ ነው የሚወለደው። አሁን የሚወለዱ ህፃናት ከወላጆቻቸው መዳፍ በላይ የሞት ተረከዝ አፍንጫቸው ስር ይርመሰመሳል። ከእናቶቻቸው ማህፀን ሲወጡ የሚጠቀለሉበት ጨርቅ አድገው ቁመቱን ሳይበልጡት ይሞታሉ። በርሱም ጨርቅ ወደ መቃብራቸው ይላካሉ። የህይወት ታሪክ የሚነበብላቸው እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። ከ - እስከ የሚባል ህይወት የላቸውም። ተወለዱ ከዚያስ? በአዋላጃቸው ሞቱ። በተፈጥሯዊ ሞት መሞት ቅንጦት እየሆነ ነው። በየመንገዱ ከገዳዮቻችን ጋር ትከሻ እየተገፋፋን እናልፋለን። አለፍ ሲልም ከገዳዮቻችን ጋርዐማዕድ እየተጋራን ነው። ያጎረሰን እጅ አንገታችንን ይፈጠርቃል። እንዲህም ሆነን ሞትን እንፈራለን። ይህ የሚያስቅ ነገር ነው'ኮ። ይህ ትውልድ በ "ጊዜ"ው ላይ ተሸንፏል። ቢያኮርፍ እንኳ የሚያባብለው የለም። ታላላቆቹ ጥይት በማንጣጣት ተጠምደዋል። ለረሀቡ ዳቦ ለእንባው ደሞ መሀረብ የሚያቀብለው ታላቅ የለውም። የኑሮ ትርምስና ውጣ ውረድ ታላላቆቹን ሽባ አድርጓቸዋል። ለመሳለም ጎንበስ ሲሉለት ኩርኩም አናቱን ያቀምሱታል። ለመማር ከእግራቸው ስር ቢደፋ ከንፅህና የራቀ እግራቸው ይሰነፍጠዋል። ይህ እግራቸው መዋል በሌለባቸው ስፍራ ስለመገኘታቸው እንደምልክት ሆኖ ይጮሀል። ትውልዱ ባክኗል! ታላላቆቹ ለሚጫወቱት ቁማር ማስያዣ ሆኗል። ህይወቱ የራሱ አይደለችም። በአራጣ ተይዛለች። በቃ አደገኛ የሆነ አዚማም ትውልድ እየተፈለፈለ ነው። የሰው ልጆች ኮቴና ጫጫታ አሁንም ከውጭ ይሰማኛል። ከዚህ ቀፋፊ ድምፅ ወዴት ብሄድ ነው መራቅ የምችለው። እንደ ጥላ ስር ስሬ ተከትሎኝ ይመጣል። አንዳንዴ እነሱን ላለማየት ስል አንዳች ስርቻ አስሳለሁ። ዓለሜን ለማጥበብ ስል በራሴ ጥጋጥግ እዳክራለሁ። የዕይታ አድማሴን ለማጥበብ ስል እጆቼን ዓይኔን ሳልጨፍን ከፊቴ ላይ አስቀምጣለሁ። የእጆቼን መዳፍ ድረስ በማየት ብቻ ዕይታዬ ውስጥ የሰው ልጆች እንዳይገቡብኝ እጥራለሁ። የሰው ልጆችን እጠላለሁ። ✨ይቀጥላል✨ #Share #like and #subscribe እያደረጋቹ። 👇Sebscribe YouTube link👇 https://www.youtube.com/@atronose

telegraph.controller.bot/files/1241158414/AgACAgQAAxkBAAKwz2qLGHM__cZgT3z3Ad4IjsQ_oIwEAAIfD2sbkFRYUCBBLI5tiDqeAQADAgADeQADPQQ
👍8❤5
August 23, 2026 2.1K