#ጥሪ_ወደ_ሞት ፡ ፡ #ክፋል_ሰባት ፡ ፡ #በአህመድ_ሁስ(ሻድ) ፧፧ ፧ ልክ አሁን ቹቻ መጥቶ እግሬ ላይ ሲቀመጥ እንደተሰማኝ አይነት ዕረፍቶች አሉ። ሲነካኝ ሲዳብሰኝ መኖሬን አረጋግጣለሁ። ነፍስ ያለው ገላ ስለነካኝ ብቻ ነፍሴ አለሁ አለሁ ትለኛለች። ከቹቻ ጋር መደባበሳችን ያድግና መላፋት እንጀምራለን። የቹቻ ሰውነት እጅግ ግዙፍ ነው።አልችለውም። ጥፍሮቹ በሞረድ የተበጁ ይመስል ስለታም ናቸው። አንዴ በድንገት አምልጠው እጄን ከቧጨሩኝ በሀይለኛው ያደማኛል። ደሜን አልጠርገውም። መላፋቱን ያቆምና ደሜን እየላሰ ይጠርግልኛል። ሚያው ብሎ አንገቱን ቀና አድርጎ ተጣራ። ጎንበስ ብዬ አየሁት። እግሬ መሀል ተመቻችቶ ድጋሚ ሚያው አለኝ። በሀሳብ ወዴት ሄድክ ይመስላል። ጭንቅላቱን ዳበስኩት። ዓይኖቹን ጨፍኖ ከውስጡ ድምፁን አጉረመረመ። ስለአንተው እያሰብኩ ነው ወዳጄ ቹቻ። ይህን አጋርነትህን መቼም ላጣው አልፈልግም። የልብህን ንፅህና ከሰው ልጆች ክፋት ጠብቅልኝ። ጆሮህንና ልቦናህን ከቃላቸው ጠብቅልኝ። ቃሎቻቸው ያፍናሉ። ልብ ላይ የሚሰነቀሩ ሹል ጦሮች ናቸው። ቹቻዬ ከህመም ሁሉ ትልቁ ህመም እነዚህን ሹለቶች መንቀል ነው። የማይሳካው ሙከራ ልብህ ላይ የተሰካኩ የቃላት እሾሆችን ለመንቀል መሞከርህ ነው። በከሰል ሻጭ እጅ ውስጥ እንደገባ ነጭ ወረቀት ነው ዕድልህ። መልክህን ይቀይሩታል። ንፁህ ልብህ በክፋት… በሴራ… በጥላቻቸው ይበረዛል። ያኔ ከጎኔ አንተንም አላገኝህም። በድመትኛ እብሪት ይይዝሀል። ገላቸው ንፁህ ከሆነ ከሌሎች የሰው ልጆች ጋር ታወዳድረኛለህ። የማወቅ የመጀመሪያው ደረጃ እጅህ ላይ ያለውን በረከትና ፀጋ ከሌሎች ጋር ማወዳደር ነው። አንተ ደሞ የውጪውን እንጂ የውስጤን የመገንዘብ ጥበብ የለህም። ዓይንህ የድመትኛ ብቻ ነው። ለዚህ ውጫዊ ውድድር ደሞ በቂ አይደለሁም። ከዚህ ወዲያ በጥላቻ ዓይንህ ታየኛለህ። የገፄ መገርጣትና የጠረኔ ስንፋጤ ይሸትሀል። ደሜን የሚልሰው አፍህ ስጋዬን ካልቦተረፍኩ ማለቱ አይቀርም። አደራህን ከሰው ልጆች ጋር እንዳታብር። እፍፍፍ..ኦ ቹቻ ፈሳህ መሰለኝ ተነስ ከዚህ። እፍፍ..የቹቻ ፈስ ረሀቤን ቀሰቀሰው። ሆዴ አጉረመረመ። ተነስቼ ቁራሽ ዳቦ ፍለጋ ጀመርኩ። መራመድ የረሱት እግሮቼ በእንፉቅቅ ከቦታው ደረሱ። የወገቤ ዘይት ተመጧል። አንድ ቀና አንድ ቋ...አንድ ቀና ሌላ ቋ...ይላል አጥንቴ። ከቀናት በፊት እንደገበሬ አርሼ ዘር የበተንኩ ይመስል ዛሬ የቤቴን ወለል እህል አስስበታለሁ። ቁጭ ብዬ እንደውሻ ባነፈንፍ በቂ ነበር። ከትንሽ አሰሳ በኋላ መደርደሪያው ስር ቹቻ ደርቆበት የተወው ግማሽ ዳቦ አገኘሁ። በሩ አጠገብ መሬቱ ላይ በተጠራቀመው የዝናብ ውሃ ውስጥ አበሰበስኩት። ሲርስልኝ አውጥቼ ግማሹን ቆርሼ ለቹቻ ወረወርኩለት። አሽትቶ ብቻ ተወው። ፡ጥጋበኛ! ዳቦዬን ይዤ ወደ ፍራሼ አመራሁ: ምናልባት ቹቻ ጠግቦ አልያም ተጠይፎ የጣለውን ቁራሽ በመመገቤ እየታዘበኝ ይመስለኛል። በውሃ የራሰ ዳቦዬን ወደ አፌ አስገባሁት። አፌ ውስጥ ሲገባ ውሃውና ዳቦው ተነጣጠለ መሰል። ውሃው አፌ ውስጥ ጠለለ። ይጣፍጣል ልበል? ተርበው የበሉት ሁሉ ይጥማል ይላሉ ። ልክ ናቸው። በጣም ርቦኝ ነበር። የተሻለ ምግብ ከበላሁ ምን ያህል ጊዜ እንደሆነኝ አላውቅም። በርግጥ በ 'ጊዜ' ማዕቀፍ ውስጥ የተቀነበበ ምንም ክንዋኔ የለኝም። ይህን ያደረግኩት በዚህ ሰዓትና ቀን ነው አልልም። ገላዬን የታጠብኩበትን… የበላሁበትን… ፀሀይን ያየሁበት… የሳቅኩበትን… ጊዜያቶች በጊዜ ማህደር ውስጥ አስገብቼ ማሰብ አልችልም። ስለጊዜ ሳስብ ገደል አፋፍ ላይ ሆነው የለቀቋት እፉዬን አስታውሳለሁ። ከዓይን እስከምትሰወር ድረስ ብቻ የምንከተላት። ከአለፈች በኋላ ምስሏ ብቻ በአዕምሯችን መዝገብ ላይ የሚሰፍር። በ "ጊዜ" ውስጥ ቁጥር አይደለም የሚቆጥረው። ጊዜ ስንል ከጧቱ ሁለት ሰዓት ከሩብ አይደለም። አልያም ሀያ ጉዳይ ለስምንት ከአርባ ሁለት ሰከንድ እያልን አይሆንም። ጊዜ ሰኞና ሀሙስ አልያም ጥቅምትና ሰኔ አይደሉም። ጊዜ ትላንትና ብለን ዛሬ ከዛሬም ደግሞ ነገ ተከታዩ አይደሉም የጊዜ መስፈሪያዎች። እኛው ነን! የሚሰፈረው በእኛ ነው። በስጋና በነፍሳችን ውስጥ ነው ጊዜ የሚሽከረከረው። በእሽክርክሪቱ መሀል የምንቆጥረው እኛ ነን። 24ቱ ሰዓታት የምንላቸው ፍካሬያቸው ከውልደት እስከሞት ድረስ ያለው ህልውናችንን ለመወከል ነው። እያንዳንዷ የግላችን ክፍል ጊዜ ነው። ህዋሳቶቻችን እንደኑግ ክምር በስጋዎቻችን ላይ ሰፍረዋል። በየሰከንድ ውስጥ ከዚህ ክምር ቅንጣት ህዋስ ትንሸራተታለች። ጊዜ ቁጥር አይደለም። ጊዜ ስጋችን ነው... ታሪካችን ነው… ህይወታችን ነው… ጊዜ እኛው ነን። ጊዜ ሀያል ነው የምንለው ባለጊዜዎቹ ሰዎች አቅማቸው ሲፈረጥም ነው። በገንዘባቸው… በስጋቸው… በስልጣናቸው… በቅቡልነታቸው… በሀሳባቸው ሲጠነክሩ በፍርጣሜያቸው በኩል ያለው "ጊዜ" አብሯቸው ሀያል ይሆናል። በፍርድ መንበሩ ላይ የተቀመጡ ተረኞች የፍርድ መዶሻቸውን ሲይዙ ጊዜ ፈራጅ ነው አልን። እኛ ነን የፈረጠምነው። ስንወድቅም እንደዚያው ነው። ጊዜ መቁጠሪያ ሰዓት… ሌትና ቀኑ… ረቡዕና ጷጉሜ ሀይል የላቸውም። እጁ የፈረጠመው እሁድ ላይ ሲሆን እሁድን ሀያል አያሰኘውም። መስከረም ፈራጅ አይደለም። ጥቅምቱ የገጠመለት ፈራጅ ሊሆን ይችላል። ጊዜ እኛ ነን ሲነሳም ሆነ ሲወድቅ በእኛ ትከሻ ላይ ነው። የጊዜ ሳይሆን የሰው ጀግና ነው ያለው። ሽንፈታችን የራሳችን ተጠያቂነት እንጂ የጊዜው አይደለም። ገጥመው የጣሉን ክረምትን አልያም በጋን ታክከው የገጠሙን ተፋላሚዎቻችን እንጂ ነሀሴ አልያም ሰኔ አልነበሩም። ምሽትን ተገን አድርገን ሀጥያት ፈፀምን... ነፍሳትን ገደልን… ዘረፍን… ብዙ ብዙ ወንጀሎችን ስለሰራን የምንጠየቀው እኛ ነን። ይህን ሁኔታ ያመቻቸልንን ምሽት ከፍርድ መንበሩ ፊት አንገትረውም። የፀሀይ መውጣትን ተከትለን ወጥተን ላስመዘገብነው ድል ነይ ፀሀይ ብለን አንሸልማትም። ጊዜ እኛ ነን። የጊዜ ጀግናም ሆነ ደካማ የለም። ይህ የኛ ጊዜ ግን መከረኛ ትውልድ ተገልጦበታል። ዘመኑ የመከራ ክርታስ ሆኗል። በዚህ ክርታስ ውስጥ ሞት… ረሀብ… ስደት… ጦርነት… ድህነት... የተባሉ ጥሬ ሀቆች ታጭቀውበታል። ይህንንም የክርታስ ቋጠሮ በእያንዳንዱ የትውልዴ አንገት ላይ እንደሜዳሊያ ተንጠልጥሏል። ለዚያም ነው ሁሉም የጎበጠው። ለዚህም ነው የድባቴ አየር ብቻ የሚነፍሰው። የዘመኔ ጨቅላዎች በእናቶቻቸው ጡቶች በኩል የሚመጠምጡት ትኩስ ደም ነው። ከፍ ሲሉ የሚታዘሉበት የአንቀልባ ዛጎሎች ቅጭልጭልታ የሚያስተክዛቸው ድባቴያም ትውልዶች በእናቶቻቸው እሹሩሩ ደረታቸውን እየመጡ ነው። የሚደልቁ ጨለማ ብቻ ዘፈን የሚታያቸው እየተወለዱ ነው። ከፍ ሲሉ ከእኩዮቻቸው ጋር የኮባ ሽጉጥ ይዘው ጥርሳቸውን ነክሰው ይታኮሳሉ። የምር ጨዋታ ሳይሆን የምር መኖር ውስጥ ናቸው። ይሄ ሁሉ ዘመኑ ላይ ያንዣበበው የሞት ጥላ ውጤት ነው። ደስታው የማይሰነብትለትን ትውልድ ማየት ያስፈራል። ሲወለድ ከእነቃጭሉ ሳይሆን ከእነድብርቱ ተብሎ የሚዘፈንለት ሆኗል። አሁን አሁን እናቶች በቀሚሳቸው የልጆቻቸውን ንፍጥ ሳይሆን ትኩስ ደም ይጠርጋሉ። አባቶች ከልጆቻቸው አናት ላይ ፎረፎር ሳይሆን የደረቀ የደም ግግር ይፈገፍጋሉ። ሌሊት የልጆቻቸው የእንቅልፍ ቅዠት አያስበረግጋቸውም። በቁማቸው የሚቃዥቱንም ተለማምደውታል።
13
2