ይዤው አፉ ላይ ሳምኩት። እጅግ የምወደው ድመቴ ነው። ስሙን ቹቻ ብዬ ብሰይመውም ፆታውን ግን እስካሁን በቅጡ አልለየሁትም። ስለድመት ብልት የማውቀው ነገር የለኝም። እንኳንስ የአንድ ተራ ድመት ይቅርና የራሴም ብልት ጠፍቶኛል። አልጋ ላይ ከወደቅኩ ዘመናት ተቆጠሩ። ቹቻ እግሬ ላይ ተቀምጦ ይተሻሸኛል። አንድ ዕለት በሬን ገርበብ አድርጌ ሳለ በተቀመጥኩበት ሰተት ብሎ ገባ። ከዚያች ዕለት ጀምሮ ስም ያወጣሁለት ብቸኛው ንብረቴ ቹቻ ሆነ። በዙሪያዬ ያለው ሁሉ በሌሎች ስያሜ ተሰጥቶት የተቀበልኩት ነው። ከዚህች ዓለም አንዱ ንብረቷ በስሜ ተመዘገበልኝ። በሬን ብከፍት የእኔን ስም እነሱ እንደማያውቁት ሁሉ እኔም መጠሪያዬን ዘንግቻለሁ። እነሆ ግን ስም ያወጣሁለት ቹቻ ከዛሬ ጀምሮ አለኝና የቹቻ ጌታ ብለው ይጥሩኝ። ግና እንኳንስ በድመት ስም ይቅርና ማዕረግ አስቀድሜ ስሜን ለዓለም ህዝብ ሁሉ ብለፍፍ ጠሪ የለኝም። ጠሪ በሌለበት ስለስም መጨነቅ ደግሞ የለየለት ሞኝነት ነው። ቹቻን ግን እኔ ብቻ ብሆንም እጠራዋለሁ። እግሬ ላይ ተቀምጦ ይተሻሸኛል። እጅግ ደማቅ የሆነ ጥቁረቱ ግርማ ሞገስ (ለድመት ግን እንደዚህ ይባላል?) ሰጥቶታል። ዓይኖቹ ቢጫ ናቸው። ከዚያች ቀን በኋላ ወደ ውጪው ዓለም አልተመለሰም። ጠዋት ሲሆን ብቻ በሩ ስርሆኖ ጭራውን እየወዘወዘ ሚያው ይለኛል። ተነስቼ በሩን እከፍትለታለሁ። በሚውልበት ውሎ ወደ ምሽት ይመለሳል ። አንዳንዴ ስጋ አልያም ዳቦ በጥርሶቹ ይዞ ጎምለል ብሎ ይገባል። አገባቡ ልክ ልጆቹን እንደሚመግብ አባወራ ነው። አፉ ላይ የያዘውን ምግብ በሩ አጠገብ ጥሎልኝ ወደ መደርደሪያው ስር ሊያርፍ ይሄዳል። ያመጣውን አንስቼ እበላለሁ። ኦ ቹቻ ወዳጄ! ከየት የሰረቅከው ስጋ ይሆን? እንኳንም ሰረቅካቸው። ፈቅደው ያልሰጡህን እንዲህ መንጠቅ ነው። ምክንያቱም የራስህ ድርሻ ነበር'ኮ ቹቻ። ማንም በራሱ ፈቅዶ አይሰጥህም። እኔም ያኔ ከዚያ ባለሱቁ ሰውዬ ዓለም ካዘጋጀችልኝ የድርሻዬን ዳቦ ሰርቄው ሮጥኩ። እንደአወቀኝ ገምቻለሁ። የእናቴን ከስራ መመለሻ ሰዓት ጠብቆ ቤታችን መጣ። በልጅሽ የተሰረቅኩት ሁለት ዳቦ አለ ክፈይ አላት። "እኔ ስሰርቅህ ብቻ ጠይቀኝ" አለችው። ሁለታችንንም በግርምት አይቶን ጭንቅላቱን ነቅንቆ ወጣ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ለእኔ ማንም ሀላፊነት እንደማይወስድልኝ ገባኝ አንዳንዴ ፍራሼ ላይ ሆኜ መደርደሪያው ስር ሙሉ ሰውነቱን አንጥፎ በድመትኛ እናወራለን። የውስጤን ሁሉ ዝርግፍ አድርጌ ስዘበዝብለት ቢጫ ዓይኖቹን ከእኔ ሳይነቅል በአትኩሮት ያዳምጠኛል። ምንም'ንኳ አንዴ ሚያው ብሎ ወደ ራሱ ዓለም ቢመለስም መደመጤ ብቻ ዕረፍት ይሰጠኛል። አንዳንዴ መፍትሄ ከሚሰነዝሩልን አፎች በላይ በጥልቀት የሚያዳምጡን ጆሮዎች ያስፈልጉናል። በመፍትሔ ሳይሆን በመደመጥ ብቻ የሚድኑ ህመሞች ብዙ ናቸው። ማቀፍ ደረጃ ያልደረሱ በመዳበስ ላይ የሚገኙ መነካካቶች ብቻ የብቸኝነትን ቆፈን ይገፋሉ። አንዳንዴ ውስጤ የብቸኝነት ዓለም ጭው እንዳለ በረሀ ይሆንብኛል። አጠገቤ ያለውን ግም ትራስ አንስቼ አቅፋለሁ። ዓይኖቼን እጨፍናለሁ። እናቴና ታናሽ እህቴ እየተሯሯጡ ወደኔ ሲመጡ ይታየኛል። የማይሮጥ እግሬን አነሳለሁ። ፈቀቅ አልልም። እህቴ ሮጣ መጥታ እግሬ ስር ትጠመጠማለች። ጎንበስ ብዬ አናቷን እስማለሁ። አፈር አፈር የሚል ፀጉሯ ይሸተኛል። ትንሽ ከብቸኝነቴ አርፋለሁ። ቀና ስል እናቴን ፈገግ ብላ አያታለሁ። የፊቷ ማዲያት አልጠፋም። እጆቼን ለማቀፍ እዘረጋላታለሁ። ወደኔ መራመድ ስትጀምር ከውጭ የሰው ልጆች ድምፅ ያውከኛል። ትራሴን ወደነበረበት እወረውራለሁ። ልክ አሁን ቹቻ መጥቶ እግሬ ላይ ሲቀመጥ እንደተሰማኝ አይነት ዕረፍቶች አሉ። ሲነካኝ ሲዳብሰኝ መኖሬን አረጋግጣለሁ። ነፍስ ያለው ገላ ስለነካኝ ብቻ ነፍሴ አለሁ አለሁ ትለኛለች። ከቹቻ ጋር መደባበሳችን ያድግና መላፋት እንጀምራለን። የቹቻ ሰውነት እጅግ ግዙፍ ነው። ✨ይቀጥላል✨ #Share #like and #subscribe እያደረጋቹ። 👇Sebscribe YouTube link👇 https://www.youtube.com/@atronose
telegraph.controller.bot/files/1241158414/AgACAgQAAxkBAAKwN2p3Zq9prC42HVkDuvYQLBrei4ccAAJYDWsbi6xRU1z6r__RmXZAAQADAgADeQADPQQ
9
3
2