#ጥሪ_ወደ_ሞት ፡ ፡ #ክፋል_ስድስት ፡ ፡ #በአህመድ_ሁስ(ሻድ) ፧ ፧ በቁሜ ኖሬ ያልጎዳሁት የሰው ልጅ ሞቼ በሬሳዬ አልበድለውም። ማንም በክብር ቢቀብረኝ ግድ የማይሰጠኝ ነበርኩ። አሁን ግን ሆዴ ባባ መሰል። ምነው ራሴ ሆይ? እስኪ ተነስቼ ይህቺን ሰላላ ሰውነት የምትሸከም ገመድ ላዘጋጅ። የማገኝ አይመስለኝም። እዚያ እቃ መደርደሪያው ስር የተጠመጠመው ሲባጎ ምንድነው? አይችለኝም? አንገቴ ውስጥ ገብቶ ያንጠልጥለኝ እንጂ እንኳንስ የተገመደ ሲባጎ ይቅርና የጫማ ክር ይገላግለኛል። ቆይ ተነስቼ ልፍታው እስኪ እስኪ? የምን ጠርሙስ ነው በመደርደሪያው ስር የሚታየኝ?እንዴ! አረቄ? አሁንስ ምድር ብትገለበጥም ግድ አይሰጠኝም። የምድራችንን ውዱን ስጦታ ይዣለሁ። መቼ ወርውሬ የረሳሁት አረቄ ይሆን? ለአቅመ ንብረት መርሳት ከደረስኩ ይደንቃል። አረቄን ይመስል የነፍስ መድሀኒቴን እንዴት ረሳለሁ? ምናልባትም ቅድም ሊሆንም ይችላል'ኮ የወረወርኩት። አልያም ትላንትና.. አልያም የዛሬ አምስት አመት.. አልያም ገና ነገ ሊሆንም ይችላል። አቦ አሁን መዘብዘቡን ላቁም። ይህቺን ውድ ፈሳሽ ይዤ እንደአበባ እቅፍ ተንከባካቢ በጥንቃቄ ወደ ቦታዬ አመራሁ። እግሮቼን አጣጥፌ ለፍርድ እንደተቀመጡ አማልክቶች ፍራሼ ላይ ተሰየምኩ። ጠርሙሷን አጥብቄ ብይዛት ተፈረካክሳ የምትደቅ መሰለኝ። ብለቃት ደግዋ ግሞ እንደእፉዬ ጥላኝ ወደ ላይ ትጓዛለች በሚል ስጋት ተጠነቀቅኩላት። ምናልባት አሁን በዚህች ደቂቃ ሞት ፊት ለፊቴ ቢመጣ እፋለመዋለሁ። በዚህች ቦታ ላይ ሆነ የምኖርለት ዓላማ አለኝ። ለአንድ ጉንጭ አረቄ ስል እስከጥልቁ እወርዳለሁ። ደረቴን ለጦር እሰጣለሁ። ለሰከንድ ዕድሜም ቢሆን የምኖርለት ዓላማ አግኝቻለሁ። ለካንስ እስከዛሬ ለመኖር የማልጓጓው ይህ የኔ ነው የምለው የዓለም ድርሻዬ ባለመኖሩ ነበር። የሰው ልጅ ከህይወት ጋር ግብግብ የሚገባ ከንብረቶቹ ጋር በወደቀው ፍቅር ምክንያት ይሆን? ክዳኑ ላይ በጥንቃቄ ቀድቼ ወደ አፌ ዋሻ ደፋሁት። በጥም የደረቀ ጉሮሮዬ መጥጦ ያዘው። ወደ ታች ወደ ውስጤ ሳይደርስ ቀረ። ሁለተኛውንም በክዳኑ ውስጥ ሞልቼ ወደ አፍንጫዬ አስጠግቼ ጠረኑን ማግኩት። የገላዬ ስስ ቦታዎች ሲነቃቁ ይታወቀኛል። ይህን ጠረን ከልጅነቴ ጀምሮ አውቀዋለሁ ከእናቴ ስድቦች እኩል ወደሳንባዬ ስመገምገው ያደግኩት ይህን ሽታ ነው። ስካር ጥሏት ልብሶቿን ስቀይርላት ሁሌ እስበዋለሁ የእሷ የግሏ ብቻ ጠረን ይመስለኝ ነበር። ከስካሯ በፊት ያላትን ጠረኗን በቅርበት ሆኜ የመገምገም ዕድሉ ስለሌለኝ ይህ አረቄ ተፈጥሯዊ ጠረኗ ይመስለኝ ነበር። ዥው ወደ አፌ! ዓይኖቼ ሲበሩና ውስጤ ላይ አንዳች እሳት ሲቀጣጠል ይሰማኛል። በመላው አካሌ እየተዘዋወረ ዳበሰኝ። ሆዴ ረሰረሰ። ጭው ያለውን የጉሮሮዬን በረሀ እንደወንዝ ሰንጥቃው ስታልፍሰ ይታወቀኛል። የጎደለኝ ይህ ብቻ ነበር? ይህ ሁሉ ድባቴ የመጣው ይህቺ ጠብታ ከህይወቴ ጎድላ ነው? አደይ ከሞላበት ሜዳ መሀል የቆምኩ ያህል ተሰማኝ። ከየት እንደመጣ ያላወቅኩት የኮረብታ ነፋስ በጆሮዬ ስር ታክኮኝ አለፈ። አንዳንድ ነብያትና መምህራን ተገለጠልን የሚሉት እንዲህ ይሆን እንዴ? ምንድነው እስካሁን ስቀባጥር የነበረው? እስካሁን የዘላበድኩትንም ትቼዋለሁ። እንደውም ሁሉ ነገር ደስ ይላልኮ። የተቀመጥኩበት ፍራሽ ምቾት..የትራሴ ጠረን..የበሩ ስር ብርሀን..በውጭ በኩል የሚተላለፉት ሰዎች ጥላ ከለር (አቤት አቤት) .. ሰዎቹ ራሳቸው..ዓለም በጠቅላላ ደስ በሚል ነገሮች የተሞላች ናት። የምን ቢራቢሮ ነች እዚያ ማዶ የምትታየኝ? ከለሯ በአየሩ ላይ ይርመሰመሳል። እንዴ! ተነሳች? እየበረረች ነው። ወደ'ኔ ስትበር መጣች። ከክንፎቿ ስር ወርቃማ ብርሀን ብልጭ ድርግም ይላል። ይሄ ሁሉ ተዓምር በጠብታ አረቂ ብቻ? የታባቱ! መመልከት አቅቶን እንጂ ውስጣችን በብርሀንና ፍቅር የተሞላ ነው። መዘርጋት ከብዶን እንጂ ሁሉም ሙሉ ነው። መዝገን የከበደው እጃችን ነው ምክንያቱ እንጂ ዙሪያችን በበረከት የተሞላ ነው። ጆሮዎቻችንን እንክፈትና የተፈጥሮን ድንቅ ሙዚቃ እናድምጥ። ቺርስ ለዓለም! ከሚስቶቻችን አንገት ስር የሚነሳው ድንቅ ጠረን ምንም ነገርን ካላስረሳን ደደቦች ነን። የባሎቻችን እቅፍ ውስጥ ተሸጉጠን ምናኔነት ካልተሰማን የአንገታችን ሀብል ይበልጠናል። የእናቶች ፍቅር ህመሞቻችንን ካላዳኑልን የአባቶች ትጋት የመኖር ወኔ ካልጨመሩልን ምንድን ነን እኛ? በቃ የሀዘን ካባችንን ወዲያ አሽቀንጥረን እንጣልና ወለሉ ላይ እንደንስ። በባዶ እግሮቻችን በመስኩ ላይእንቦርቅ። ነገን ለራሱ ነገ ትተን ዛሬን እንኑር። አቦ በቃ እንፍታታ። ቺርስ ለዓለም! እጃችንን አፍንጫችን ስር አድርገን ትንፋሻችንን እንሞክር። ይነፍሳል? ልባችን ስር እጃችንን ወትፈን ምቱን እናዳምጥ። ይቆጥራል? ብብታችን ስር ላባችን እየፈሰሰ ነው አይደል? በዛሬ ላይ ምላሳችንን ለማውጣት ከዚህ ወዲያ ምን ያስፈልገናል። ነገ የኛ አይደለም። ዛሬ የወገባችንን መቀነት እንፍታው። የሱሪያችንን ቀበቶ እንበጥሰው። ገላችን ላይ ምንም አይረፍ። እንደ ልጅ መለመላችንን እንፈንጥዝ። ነፍሳችን ትቦርቅ! ሶስተኛዬን ይሁን አራተኛዬን አላውቅም ክዳኑን አንስቼ ልቀዳ ስል ጠርሙሱ ባዶ ሆኗል። እናትሽን ዓለም! ለዚህች እ'ልፍ ለምትል የአፍታ ደስታሽ ገደል ግቢ። የዚህች ዓለም ደስታ እንደዚህ የጤዛ ዕድሜ ነው ያላት። በረሀ መሀል እንደተቀመጠ በረዶ አለ ስንል የለም። ለዚህ ነው ሁሌም ከሞት በፊት ያለ ደስታ የሐሰት ነው የምለው። ፌሽታው ያለው እቃቃ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ብለን የደረደርነውን መጫወቻ ስናፈራርሰው ነው። ይህ መፈራረስ ደግሞ ታላቁ ሞት ነው። ከእሱ በኋላ ነው እውነተኛው ደስታ የሚቀጣጠለው። እጃችን ላይ ባለው ማንኛውም በረከት አንርካ። ቅድም ጭላጭ አረቄ ሸውዳኝ ዘላበድኩ። የሌለ ሀቅ በአንድ ጉንጭ አረቄ ተደልዬ ቀጠፍኩ። ይቅር በለኝ ራሴ! የሰው ልጅ ደስታውን የሚያጣው እጁ ላይ ያሉትን ስጦታዎች አቆይቶ ለመጠበቅ በሚያደርገው ውጣ ውረድ ነው። በቃ እንልቀቃቸው። በረከቶቻችን እውነትም የእኛ ከነበሩ ይሰንብቱ። ካልሆነም ከእኛ ይራቁ። እንዲሁ ሌጣችንን እንሁን። እናትሽን ዓለም! እጄ ላይ ያለውን የአረቄ ጠርሙስ ዘቅዝቄ የምላሴ ጫፍ ላይ አስጠጋሁት። ባዶ አየር ብቻ። ውረድ... ውረድ... ውረድ... ውረድ... ዓለም ስካሯንም ረብ ካለው ፍሬዋ እኩል ከለከለችኝ። የጠራ ምስሏን አላይላት ስል ብዥታዬን ነሳችኝ። አንቺ እርጉም ስካሬን እንኳ ተይልኝ። ከእነክብሬ ሆኜ ያልሰጠሽኝን ፊትሽን ተልከስክሼም እንኳ አትንፈጊኝ። አንቺ ዓለም ስለተልከሰከስሽ ነውም ክብሬን ጠብቄ እንኳ ያላገኘሁሽ። እንደምንም ብላ ዝንብ የምታህል የአረቄ ጠብታ የጠርሙሱ ከፈፍ ላይ ተንጠለጠለች። ዓለም በምላሿ በዚህች ጠብታ በኩል መሀል ጣቷን ያወጣችብኝ መሰለኝ። ጠርሙሱን እጄ ወደ መራኝ ወረወርኩት። ከመደርደሪያው ጀርባ ወዳለው ግድግዳ ሄዶ ተላተመ። በዚህ ድምፅ የደነገጠው ድመቴ ከመደርደሪያው ስር ወጣ። ኦ ቹቻ ወዳጄ! እስካሁን ድምፁን አጥፍቶ ተኝቶ ኖሯል? ሚያው እያለ ወደ ፍራሼ መጣ። እሱም እንደኔ ብዙ ሰዓት መኝታው ላይ ስለነበር ሰውነቱ አልታዘዘለትም መሰል መሳብ ይቀናዋል። መሀል ጉዞው ላይ የፊት እግሮቹን ለጥጦ ደረቱን ወደ መሬት በመለጠፍ ተንጠራራ። እግሬ ስር ተሻሽቶ ተንጠራርቶ ጅራቱን ነቀነቀ።
15
2