አትሮኖስ: post #95260 — TG.ME

​​የሰው ልጅ ለብቻው የመቆም ፍርሀቱ ከሞቱ በኋላም ይሻገራል። ብሞት ማን ይቀብረኛል በሚል ስጋት በቁሙ ሳለ ህብረት ይመሰርታል። ለሞተ ስጋው እንኳ ብቸኝነትን አጥብቆ ይፈራል። ህብረት የሚመሰርተው ራሱን ከአውሬ ለመጠበቅ አይደለም። ከመሰሎቹ የሰው ልጆች ጥቃት ራሱን ለማዳን ነው። አጠገባችን የምንፈራው ወዳጃችን እኛንም በተመሳሳይ ይፈራናል። ያለን አማራጭ ማህበራዊ ህይወት በሚል መሸንገያ የሚፈራውን መሰሉን በቅርበት መከታተል አለበት። የሰው ልጅ በመንፈስም ሆነ በስሜቱ ጠንካራ ነው የምለው ራሱን ከመንጋው ሲነጥል ነው። በሩን ቀርቅሮ ድሉንም ሆነ ሽንፈቱን ለብቻው ማጣጣም ሲችል ነው። ቀዝቃዛ ነኝ። ለድሌ ጭብጨባን ለሽንፈቴ ደግሞ ቁጭት የማሰማ ልፍስፍስ አይደለሁም። አየሩ በሙቀት እየወበቀ ነው። ከላዬ ላይ የደራረብኩትን ሁለት ወፍራም ብርድ ልብሶች አስተካክዬ እስከ አገጬ ስር ተከናነብኳቸው። ላቤ በወገቤና ብብቴ ስር እየፈሰሰ ነው። ስንት ሳምንት ሆነኝ ግን ገላዬን ከታጠብኩ? እንጃ ቀን መቁጠር አቁሜያለሁ። ገላዬ ነግቶ በመሸ ቁጥር በላብ ይታጠባል። እንደ ድመት ገላ ራሴን በራሴ አፀዳለሁ። ከዚያ ባለፈ ግን ውሀ ከነካኝ ቆየ። እጄን ወደ ብብቴ ስር አስገብቼ ከላብ ባህር ጠቅሼ አወጣሁ። ወደ አፍንጫዬ ሰድጄ ጠረኑን ማግሁት። ጠረኑ ይህን ይመስላል ብዬ የማመሳስልለት ሌላ የማውቀው ጠረን እንዳለ ብዬ አሰብኩ። ጠፋ። ምናልባት ግን የሰካራም ሰው ሽንት ትንሽ የሚቀርበው መሰለኝ። ምን አገባኝ አሁን ለሚሞት ገላ ጠረን ለምን አስባለሁ? ገናዤ ይጨነቅበት። ከፈለገም ወደዚያ ውሰዱና ጥምብ አንሳ ይገላግለው ይህን ሬሳ ይበል። ከሞቴ በኋላ ለሚፈጠረው ነገር እኔ ምን አገባኝ። በርግጥ በህይወት እያለሁም ከዚህች ዓለም ድርሻ ስር አልተራከብኩም። እንዲያውም ስሰጣት ኖሬያለሁ። ውለታ የዋለላትን አመድ አፋሽ ታደርጋለች። ከፈለጉም ቄራ ካለው የከብት ማረጃ ያስገቡኝ። እዚያ ሰውነቴን በብልት በብልቱ እየለያዩ ለሚያስፈልጋቸው የሰው ልጆች ይስጧቸው። የተንሻፈፈና ወደ ቀኝ ሲሉት ግራ የሚረግጥ እግር የሚጠቅመው ካለ ይውሰድ። በሀዘንና ጭንቀት የታፈነ ልብ ለሚፈልግ ካለ ፈቅጃለሁ ይሰጠው። አንዳንዴ ስለጥርስና እግሮቼ አስባለሁ። ከኔ ጋር ስለመኖራቸው ትርፍና ኪሳራ አሰላለሁ። ሰውነቴ ላይ ተጣብቀው ከመኖር ውጭ ምንም የሚፈይዱት ጉዳይ የላቸውም። ገና ለገና ስጋዎችህ ነንና ሸክምህን እናብዛው ብሎ ነገር የለም።ጥርሶቼን ስቄባቸውም ሆነ  የረባ ምግብ  አላምጬባቸው አላውቅም። የሚያስቀኝ ጉዳይ ቢገጥመኝ መሳቅ የምችል አይመስለኝም። ጥርሶቼ ለሳቅ ባዳ ናቸው። እርስ በርሳቸው እየተፋተጉ ሲንቀጫቀጩ ነው የኖሩት። በውሃ እየራሰ ለምበላው የበሰበሰ ዳቦ ረጋጭ ጥርስ አያሻኝም። ጥርሶቼ ምናልባት ሊሰሩ የሚችሉ ነገር እልህን መንከስ ብቻ ነው። ሌላው ኪሳራ ደግሞ እነዚህ እግሮቼ ናቸው ከገላዬ ትልቁ ስራ ፈት ሰውነቴ ነው።  የሚሮጥበት መስክ የሚራመድበት ጎዳና የለውም። ጉዞዬ ሁሉ የእንፉቅቅ ነው። መራመድ የሚጠይቀኝ የጉዞ ርቀት በህይወቴ ውስጥ የለም ። የሚፈልጋቸው ካሉ ቆርጬ ልሰጠው ፍቃደኛ ነኝ። ወስዶ መራመድን ያሰልጥናቸው። ከጎዳናው ጋር ሀ ብሎ  ያስተዋውቃቸው። እኔ በደረቴ ብሳብ ካሰብኩበት እደርሳለሁ። እኔ አሁን መሞት አለብኝ። ከዚህም በላይ ብኖር ደስ ይለኛል'ኮ ግን ሬሳዬን ለሚገንዙት ሰዎች ከዚህ በላያ ማግማት ተገቢ መስሎ አይታየኝም። የብብቴንና የብልቴን ዙሪያ ፀጉር በመመንጠር ላደክማቸው አይገባም ቶሎ ራሴን ልገላግልላቸው። በቁሜ ኖሬ ያልጎዳሁት የሰው ልጅ ሞቼ በሬሳዬ አልበድለውም። ማንም በክብር ቢቀብረኝ ግድ የማይሰጠኝ ነበርኩ። አሁን ግን ሆዴ ባባ መሰል። ምነው ራሴ ሆይ? እስኪ ተነስቼ ይህቺን ሰላላ ሰውነት የምትሸከም ገመድ ላዘጋጅ። የማገኝ አይመስለኝም። እዚያ እቃ መደርደሪያው ስር የተጠመጠመው ሲባጎ ምንድነው? አይችለኝም? አንገቴ ውስጥ ገብቶ ያንጠልጥለኝ እንጂ እንኳንስ የተገመደ ሲባጎ ይቅርና የጫማ ክር ይገላግለኛል። ቆይ ተነስቼ ልፍታው...... ✨ይቀጥላል✨ #Share #like and #subscribe እያደረጋቹ። 👇Sebscribe YouTube link👇 https://www.youtube.com/@atronose

❤13👍7🥰3🤔3🔥1
August 10, 2026 3.9K