እነዚያን የፀሃይ ቀለበቶች ከወለሉ ላይ ፈለግኳቸው። ሁለቱም የሉም። በእርግጠኝነት በበሩ ስር የሚገባው የውሸት ዓለም ብርሀን ውጧቸዋል። ቀለበቶቹ እናቴንና ታናሽ እህቴን መሰሉኝ። ትንሽ ብቅ ብለው የጠፉ የብርሃን ገላዎች። ቀለበቶቹም እነሱም ጠፍተዋል። በዚህ ምድር ላይ መቆየት የነበረባቸውን ያህል ጊዜ ሳይኖሩ በውሸቱ ዓለም መንጋጋ ውስጥ ተሰለቀጡ። ይህች ዓለም የባለአቅሞች ናት። ጉልበት አልባ ልፍስፍሶች የመኖር ዋስትና የላቸውም። በርግጥም ለመኖር አንዳችን በሌላችን መበላላት ግድ ይለናል። ሜዳው የታጋዮችና አሸናፊዎች ሆኗል ። ይህም የዓለምን ሚዛን ለመጠበቅ ይበጃል። ያሸነፉት ብቻ ቢሞሉ ምድራችን ትልቅ የእህል ቅሪላ ትሆናለች። ለተሸነፉት ብቻ ብንለቅ የጥምብ አንሳዎች መናኸሪያ መሆኗ ነው። ይህን ተቃራኒ ፅንፍ የሚጠብቅልን ይኸው የጉልበተኞች ደካሞችን የማጥፋት ዘመቻ ነው። በዚህ መርህ መሰረት ካልተጓዝን መቼም ቢሆን አንሰነብትም። ደካሞችን አዝነንላቸው ብናቆያቸው ቀስ እያሉ የሚበሉን ራሳችንን ነው። በተቻለን መጠን በገንዘብ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ቅቡልነት ዘንድ ራሳችንን ከማንም በላይ ማፈርጠም ግድ ይለናል። እናቴና ታናሽ እህቴ ጋ የተለያየሁት በዚሁ የሌሎች ፈርጣማ ክንድ ነው። የዓለማችን ህጎች በሙሉ የተደነገጉት በባለአቅሞ ትከሻና ቁመና ልክ ነው። ደካሞችን ለመግዛት አመቺ ሜዳ የሚደለድል ስርዓት ውስጥ ነን። ፍትህ ብሎ ቀልድ አይጥመኝም። የኮረኮመኝ እኮረኩማለሁ። ለሰደበኝ ፈገግታን አልመልስም። ክብሬን እየነካ ጭራዬን አልቆላም። በርግጥ ከዚህ ደረጃ የሚያደርሰኝ የህይወት መስተጋብር ከሌሎች ጋር ባይኖረኝም ፍትህ ይሉት የልጆች ጨዋታን አልቀበልም። ህግ ትልቁ የሰው ልጅ ትንሹን የሰው ልጅ ለመርገጥ ያመቻቸው ርብራብ እንጨት ነው። ደሀዎች የምድራችን ምስጦች ናቸው። ሌሎች ያፈሯቸውን ሀብቶች እንባ በመዝራት ያጭዱታል። ምናልባት ይህ የምስጥ መንጋ ህብረት መስርቶ አደባባይ ላይ ሰልፍ ቢወጣ ባንዲራውን የምይዝለት እኔ እሆናለሁ። የደሀዎች አደገኛው ደሀ ነኝ። ብሆንም ሌሎች ሰርተው ያመጡትን ዳቦ ለምኜ አልቀበልም። በድካም ረመጥ ውስጥ አልፈው ያመጡትን ተርመጥምጬ አልወስድም። ምናልባት ግን ዕድሉን ካገኘሁ እሰርቃለሁ።መለመን ነውር አድርጎ መዝረፍን ያበረታታ ሀሳብ ይጣረሳል መሰል። ነገር ግን በዚህ ሀሳቤ ውስጥ አንድ እውነት አለ። የሰው ልጆች በላባቸው ደክመው ያመጡትን ዳቦ ሳያውቁ ከምሰርቃቸው በላይ ለምኛቸው በፍቃዳቸው የሚሰጡኝ ዳቦ ይጎዳቸዋል። በፍቃዳቸው ሲሆን ከአስሩ ላይ አንዱን ሲሰጡኝ ዘጠኝ ቀረኝ ብለው ይቆጥራሉ። ይሄ ደሞ የኋላ ኋላ ያስቆዝማቸዋል። ክንዴን በምላጭ ቆረጥኩት። ይህ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ አላውቅም። ብዙ ጊዜ ደሜ በሚደርስብኝ የስሜት ውጥረት በመነሳት እሳት ላይ እንደተቀመጠ ወተት ይንተከተካል። ይህን ጉልበቱን በዚህ መንገድ ማስተንፈሻ ልፈጥርለት ይገባል። ምላጭ ለውስጣችን ረብሻና ሁከት እንደማሪያም መንገድ አይነት ነው። ብዙ የምላጭ ምልክቶች የታተመበትን ክንዴን አየሁት። ለዶሮ የተበተኑ ጥሬዎች ይመስላሉ ጠባሳዎቼ። እዚያም እዚህም ቆስለዋል። አሁን የጫርኩት ቁስል ደሙ እየወረደ ነው። በመርፌ እንዳፈነዱት የፊኛ ኳስ ውስጤ ሲረግብ ይታወቀኛል። የውስጤን ቁስልና ህመም ደሙ አርግዞት ሲፈስ አየዋለሁ። ስፍገመገምበት ከነበረው የተራራ ጫፍ ወርጄ ከመሬቱ ላይ እርፍ ያልኩ ይመስለኛል። ደም እንደ ምስ ነው። በተገቢው መንገድ ያልፈሰሰ ያሰክራል። ያልከፈክፋል። በራሱ ሁኔታ የተቅበዘበዘውንና እዚህም እዚያም የምትረግጥን ማረፊያ አልባ ነፍስ ግን በተገቢው መንገድ ያፈሰስንላት ደም እርፍ ያደርጋታል። ያሰክናታል። ደስታ የሚገኘው ጥልቅ ከሆነ ሀዘን ውስጥ ነው። ቁስላችንን ብንነካካው እንዲህ ያለም የለ የሚያሰኝ የነፍስ መፍነክነክ ውስጥ እንገባለን። ከድባቴያችን ጀርባ የጎላ ፈንጠዝያችን አድፍጧል። የሰው ልጅ የተፈጠረው እኛ ሀዘን፣ ቁስል፣ ህመም ብለን ለምንጠራቸው ስሜቶች እንዲገዛ ነው። ከእነዚህ መስተጋብሮቹ ጀርባ ትንሽ ቢመረመር ነፍሱ እየቦረቀች ነው። ኩልል ያለችው የደስታው ኩሬ ከእያንዳንዱ ሲቃዎቹ ጀርባ ትገኛለች። ሲወለድ በእናቱ ምጥና ህመም ውስጥ የተገላገለ ነፍስ በምድር ላይ ሲኖርም ከሚያጋጥሙት ምጥና ህመም ደስታውን ያዋልዳል። ይህ ማንም ያልነገረን የደስታ ኬሚስትሪ ነው። ለዚህም ነው ጥልቅ እውነተኛን ሀሴትና ዕረፍት ስፈልግ ከክንዶቼ ላይ በምላጭ የምጭረው። ንቧ ማሯን ለማምረት የአበባዋ ደረት በንቧ ሹለት መወጋቷ ግድ ነው። ከህመሞቻችን ፥ መታደሳችንን ... ከሲቃዎቻችን ሳቆቻችንን ከሽክረቶቻችን መለስለሳችንን ከመውደቃችን መነሳታችንን ከሀዘናችን ፥ ፈንጠዝያችንን እናዋልድ። የውልደታችንና ህያው የመሆናችን ምልክት ለቅሷችን ብቻ ነው። ሲያዋልዱን ከእናቶቻችን ማህፀን ስንወጣ ካላለቀስን መኖራችን ያጠራጥራል። ጤነኝነታችን ይመረመራል። በአዋላጆቻችን እጅ ደረታችን በሀይል ይደበደባል። ያኔ ማልቀሳችን ይጀምራል። አሁን እልልታ ያሰሙልናል። ይህ ሁሉ ግርግር የቀሪው ህይወታችን ፍካሬ ነው። መኖር ስንሻ እምባችን መውረዱ ግድ ይላል። ሳቆቻችን ሲበዙ የአዕምሮ ጤናችን ሁኔታ ይፈተሻል። ብዙ ሳቅ የአዕምሮ እክል ምልክት ይመስላል። ይህ ጥሬ ሀቅ እኔ ጋር ከፍ ብሎ ይሰራል። ቤቴን በአትኩሮት ገረመምኳት። ካለ'ኔ ማንም ገብቶባት አያውቅም። የእቃዎቹ ነጠላነት ይህን ያሳያል። አንድ ብርጭቆ… አንድ ሰሀን… አንድ ማንኪያ … አንድ… አንድ... አንድ እኔ። የህፃን ልጅ አልጋ የምታክለውን ይህቺን ክፍሌን ማንም እንዲረግጥባት አልፈልግም። ብችል ግድግዳና ጣራዬን ነቅዬ ከአንዱ የሰው ልጆች ከማይደርሱበት የዓለም ጥግ ብተክላት እመኛለሁ። የጣሪያዋ ከወለሉ በጣም መራቅ ዕድል ለአንዳች ውሳኔዬ ያመቻቸልኝ ነገር ያለ ይመስላል። አዎ ማንንም አልፈልግም። በዚህ ፍቅር፣ ጓደኝነት፣ መተሳሰብና ውዴታ ጠፍተው የውሸት አንድነት ፍንትው ባሉበት ዘመን የማንንም ፊት ሳሟሽ አልኖርም። ከማንም ጋር ህብረት ፈጥሬ የነፍስ እከክን መጋራት አልሻም። የሰው ልጆች ቃል ያድናል አልያም ይገድላል። የሚያድንበት አጋጣሚ በመዳኑ የአዳኙን ውለታ መመለስ ለሚችል ብቻ ነው። ካልሆነ ይህን ዕድል አታገኘውም። ከአንተ አንዳች ጥቅም የማያገኝ ሲመስለው ግን የውስጥ አካልህ ድረስ ዘልቆ የሚያደባይህን ቃል ያወርድብሀል። ከአንተ አልፎ አበቦችን የሚያረግፍ የሰው ልጆችን ቃል እንዲህ ጥግ ይዘው ካልሸወዱት አይሆንም። የእናቴን ማህፀን ብቻዬን ነው ረግጫት የወጣሁት። በዚያን ወቅት ይህ የማህፀን ውስጥ ትግል እጅግ ከባዱ ነበር። በዚያች አቅሜ ያንን ሁሉ የስጋ ግድግዳ አልፌ ለዚህ ከበቃሁ ይህ አይከብደኝም። ያኔ'ኮ ነፍስ አይታወቅም ይህን እንዴት ማስታወስ ተቻለኝ? የዛሬ ፈተና ሁሉ ነገ ይረሳል እላለሁ። ስለዚህ ማንም ፈተናዬንም ሆነ ድሌን እንዲካፈል ዕድል አልሰጥም። ማህበራዊ ህይወት የሚሉት ግምነትን የመካፈል መርህ አይደላኝም። መቻቻል በሚል ስያሜ ጫንቃዬ ላይ የማንንም ቂጥ አላስቀምጥም። እኔም በማንም ትከሻ ላይ ጥላዬ እንኳ እንዲያርፍ አላደርግም። የሰው ልጅ ብቻውን የመቆም ፍርሀቱ ወደ ህብረት ኑሮው ይወስደዋል። ነጠላ ሆኖ መቆም በመሰሎቹ ያስበላዋል። የሚበላውን መንጋጋ ደግሞ ማህበራዊ ህይወት በሚል ሰበብ በቅርበት ለመከታተል ያስችለዋል።
16
3