#ጥሪ_ወደ_ሞት ፡ ፡ #ክፋል_አምስት ፡ ፡ #በአህመድ_ሁስ(ሻድ) . በዚህች ምድር ላይ በብቸኝነት አለቺኝ የምላት ይህቺን ታናሽ እህቴን ብቻ ነው። እንደ ልጅ ስትፈጥን አይቻት አላውቅም ። ድምጿ ሁሌም ለሆሳስ ነው። ቀይና ክብ ፊቷ ሁሌም በአርምሞ ባህር ውስጥ ይዋኛል። እንደልጅነቷ አንድም ቀን ተቃውማ አታውቅም። ተነሺ ስትባል"እሺ" ሂጂ "እሺ" ይህን አድርጊ "እሺ" ከማለት የዘለለ ቃል አይወጣትም።ሁሌ አዘውትራ ከምትለብሰው ቢጫ ሙሉ ቀሚስ ጋር ሳያት ክንፏን የተሰበረች ቢራቢሮ ትመስላለች። ደግሞ እንዴት አይነት ቆንጆ እህት ነው ያለኝ። ትክዝ ብላ ስትቀመጥ ሁኔታዋን አጤናለሁ። ድንገት ቀና ስትል እሷ ላይ የተተከሉ ዓይኖቼን ትይዛቸዋለች። ጥርሷን ሳትገልጥ ፈገግ ትላለች። እደነግጣለሁ! የሆዴ ረሀብ እየበረታ ነው። ክፍሌ ውስጥ የሚበላ ነገር ተነስቼ ለመፈለግ ብርታቱ የለኝም። ቢኖረኝም የደረቀ ቁራሽ ዳቦ ነው የማገኘው። እሷን በሩ አጠገብ ወለሉ ላይበተጠራቀመው የዝናብ ውሃ አበስብሼ እበላለሁ። ከመሬት የወደቀን መብላት በልጅነቴ የለመድኩት ነው። አንድ ዕለት እናታችን ድግስ ላይ ውላ መጣች። ትንሽም ቢሆን አለባበሷ ተቀይሯል። እንደለመደችው አረቄዋን መጠጣት ጀመረች። እኔና ታናሽ እህቴ ሆዳችን ምግብ ካገኘ ብዙ ሰዓታት አልፏል። እህቴ በረሀብ ተዳክማለች። ከንፈሮቿ ደርቀዋል። ይህን ረሀባችንን ለእናታችን መንገር አንችልም። ፈርተናል። አረቄው የተለመደ ስድብና እርግማኗን ማውረድ አስቻላት። "እናንተ ዲቃላዎች! እንደሱ አትዩኝ" አለችን። ቀና ብለን አየናት። "እናንተ የተረገማችሁ! አንድ ቀን ግን እቀጣቹሀለሁ" ብላ እጇን እንደመንከስ አድርጋ በእልህ ታሳየናለች። የተለመደ ሁኔታዋ ስለሆነ በእዝነት ከማየት ውጭ አንፈራትም። በዚያች ምሽት ግን ያለመደባትን ተዓምር አየን። እንባ! ለመጀመሪያ ጊዜ እናታችን ዓይኖቿን እኛ ላይ በስስት እያንከራተተች ስታለቅስ አየናት። በምሽት የፀሀይ መውጣትን የመሰለ ተዓምር ሆነብኝ። ከዚህም በላይ ያስደነቀኝ ሌላ ተዓምር ተከተለ። እግሯ አጠገብ የነበረችውን እህቴን አናት ዳበሰች። በር ከፍቼ ወጥቼ አደባባይ ላይ መመስከር ፈለግኩ። እነሆ የእናቴ እጆች ዳበሱ። ፍቅርንም መዝራት የሚችሉ ድንቅ ተዓምራት ናቸው። እነሆ እናንተ ከንቱዎች የእናቴ ዓይኖች የስስትን ጨረር መበተን ይችላሉ። እኔንም እያየችኝ "ልጆቼ ክፉ ነኝ! እዚህ አንጀታችሁ በረሀብ ታጥፎ እኔ ግን የማንንም ድግስ ስቀላውጥ ዋልኩላችሁ። አሳማሚ ቅጣት ይገባኛል ልጆቼ። ከአልጫው ከቀዩ እያደረጉ ሲያስመርጡኝ እናንተን ዘንግቼ ከርሴን ስሞላ ቆየሁ" በስካር በተቆላለፈ አንደበቷ ምራቋ በአፏ ስር እየወረደ አለቀሰች። "እጄ ላይ ያስቀመጥኩት ነጭ ሰሀን የእናንተን መልክ ሊያስታውሰኝ እንኳ አልቻለም። ደሞ ሙሽራዋ እኔ እለብስ የምመኘው አይነት ቬሎ ለብሳለች። የራሴን ህልም በእሷ ውስጥ አየሁባት። አባታችሁ ከጦር ሜዳ ሲመለስ እንዲህ ነበር ሊያገባኝ ያቀደው። ደሞ ሱፍ በእርግጠኝነት ያምርበት ነበር። ከረባት ባያስርም ግድ አይሰጠኝም ነበር። ጥርሶቹ እያሉልኝ። በቃ እነሱን ሳያቸው የራሴ ሰርግ መሰለኝ። ብዙ በላሁ ልጆቼ። አማርጬ በላሁ ልጆቼ ይቅር በሉኝ" እንባዋ አልቆመም። ታናሽ እህቴን ከእግሯ ስር ገፋ አድርጋት ተነሳች። "ክፉ ነኝ! ክፉ ነኝ!'' እያለች በሩን ከፍታ ወጣች። እዚያው ደጃፍ ስር ቁጭ ብላ ጣቶቿን አፏ ውስጥ ወተፈቻቸው። ዓይኖቿ ፈጠጡ። ትንፋሽ እስከሚያጥራት ድረስ ሆዷ ወደ ደረቷ ተሳበ። ዓይኖቿ እምባን አዘሉ። ሙሉ ሰውነቷ ተርገፈገፈ። ልቧ ልትወጣ የፈለገች ይመስል ትሰብቀዋለች። ወደላይስትጨነቅ ነፍስ ደረቷን ተመለከትኩ። የበላችው በሙሉ መሬቱ ላይ ተዘረገፈ። ደረቷን ታቅፋ እንጥፍጣፊ የምግብ ቅሪት ካለ ትገፋለች። አቅም አጥታ እዚያው ቁጢጥ ባለችበት ከመሬቱ ላይ ተዘረፈጠች። ፊቷ በላብ ረስርሷል። ስስ ፀጉሯ በላቧ ረጥቦ ግንባሯ ላይተለጥፏል። ይህቺን ጉርሻ ከሆዷ ለማውጣት እንዲህ ሲቃ ውስጥ ከገባች እኛን ለማውጣት ማህፀኗን እንዴት ተሰቃይታ ይሆን? ብዬ አሰብኩ። የበላችው በሙሉ ከወጣ በኋላ ንፋሱ እንደተነፈሰለት ፊኛ ሟሸሸች። የዚህች ሴት ነገር የበለጠ እየገረመኝ መጥቷል። እሳትና ውሃ በአንድ ላይ የሰፈኑባት ሁለቱም መውጣትና መገለጥ ባሻቸው ሰዓት ሳይነካኩ በግብሮቿ በኩል ሲወጡ አያለሁ። በእጆቿ አንቃኝ ልትገለኝ ብትሞክር እንኳ እየሞትኩ ዓይኖቿ ውስጥ ጥልቅ ርህራሄን አይባታለሁ። ድንገት ከተቀመጠችበት ተነሳች። ጥርሶቿን ገልጣ ባትስቅም ፊቷ ላይ የቅድሙ ሀዘን የለም። ፊቷ ፈክቷል። ወደ እቃ መደርደሪያው ፈጠን ፈጠን ብላ ተራምዳ አንድ ዝርግ ሰሀን አውጥታ ወደ ደጅ ተመለሰች። አስታውካ ወደ ተፋችው ምግብ ሄዳ መልቀም ጀመረች። ልክ ያልሆነ ነገር ተሰማኝ። የሆነ የተዘበራረቀ የህይወት መልክ በእኔ፣ በታናሽ እህቴና በእናቴ በኩል ሲኖር አስተዋልኩ። ልክ ባልሆነ የህይወት መድረክ ላይ እየተወንን ነው መሰል። ከጓዳ በኩል ብቅ ብሎ "አቁሙ! ትንሽ ዕረፍት ወስዳችሁ ዳግም ትመለሳላችሁ" የሚለን የትወና ባለሙያ ይወጣል ብዬ ጠበቅኩ። ዙሪያዬን አሰስኩ ምንም ሸምድደን ያስቀመጥነው የቃለ ተውኔት ወረቀት የለም። በቃ። ይህ ሀሰተኛ ድርሰት ሳይሆን በእናትና ልጆች መሀል እየተኖረ ያለ ጥሬ የህይወት ሀቅ ነው። ያስታወከችው እናቴ ብቻ አይደለችም። ህይወት ጭምር ናት በእሷ በኩል ቅርሻቷን ያሳየችን። አንዳንዴ ከሞት እውነተኛ ቅጣት ይልቅ የህይወት ሐሰተኛ ቀልድ ውስጥን ያደማል። የዚያች ቀን ሁኔታ ልቤ ስር ንቅሳት ሆኖ ተቀምጧል። አዕምሮዬ ተሸክሞት ትዝታ ሳይሆን ልቤ ላይ ቁስል ሆኖ አርፎ አሁን ደም ከእሱ ቁስል በኩል ይረጫል። አፈርና ድንጋይ እንዳይቀላቀልባት በጥንቃቄ እየመረጠች ወደ ሰሀኑ ትጨምራለች። ጥርሶቿ በእልህ ይንቀጠቀጣሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ እናቴን ፈራኋት። ዝርግ ሰሀኑን ይዛ "ተነሱ እንጂ ልጆቼ ታጠቡ እጃችሁን እኔ እናታችሁ ቆንጆ ምግብ አመጣሁላችሁ'' ብላን ሰሀኑን ይዛ ፊት ለፊቴ ተቀመጠች። ተነሳሁ። ስቆም ሰሀኗንና እሷን ተመለከትኳቸው። የሰሀኑ ስፋትና ከላይወደታች የሚታየኝ የእናቴ አናት ስፋት እኩል ለእኩል ነው። ሁለቱም ተላምጦ የተተፋ ህይወትን ተሸክመዋል። እኔና እህቴ ወጥተን እጆቻችንን ታጥበን ቀረብን። እናቴ አይኖቿን አሁንም አሁንም ታብሳለች። ታናሽ እህቴ ከቀረበው ምግብ ላይ እጆቿን ለመዘርጋት ጓጉታለች። ስለቀረበላት ነገር አታውቅም። ሰሀኑን አየሁት። በቢጫና ግራጫ ከለር የተሞላ ተላምጦ ያልደቀቀ የስጋ ክምር። "ብሉልኝ እንጂ ልጆቼ" አለች ሳግ ባነቀው አንደበት። ሶስታችንም እጆቻችንን ዘረጋን። ልክ ትልቅ ድግስ እንዳሰናዳች ሁሉ ሽርጉድ አበዛች። የኔ እናት! ሁኔታዋ መሬት ላይ ያስመለሰችውን አፍሳ ያቀረበችልን አይመስልም። ህይወት ግን ምነው እንዲህ ቀለለች። አልከበር አለች። በቀኝ ሲሏት በግራ ብቅ እያለች ድብብቆሽ ልጫወት ብሎ ቅለት። እናቴ አሁንም አሁንም ብሉልኝ እንጂ ልጆቼ እያለች በስስት ዓይን ታየናለች። ይህን አይነት አስተያየቷን ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ተመለከትኩ። ለካንስ የምትሰጠው አጥታ እንጂ አሰጣጡንና ፍቅር ማሳየቱን ትችልበታለች። እኔም ከቀረበው ማዕድ ቆነጠርኩ። በአረቄ ቃና የታጀበው የስጋ ቁርጥራጭ አፌ ውስጥ ፈራረሰ። ታናሽ እህቴ በጉጉትና መንሰፍሰፍ ውስጥ ሆና ትጎርሳለች። ምናልባት ነፍስ ካወቀች ወዲህ ይህ የመጀመሪያዋ የስጋ ቅምሻ ይመስለኛል። የህይወት ስላቅ በዚሁ ከቀጠለም ይህ የመጨረሻዋ ሆኖ ይጠናቀቃል ብዬ ሰጋሁ።
19
2
1