ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት አባታቸን በጎችን ሲጠብቁ ሌሎች እረኞች በአመጻ ከሰው ሰርቀው ቆርጠው ያመጡትን… — "፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel — TG.ME

.......➯ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት አባታቸን በጎችን ሲጠብቁ ሌሎች እረኞች በአመጻ ከሰው ሰርቀው ቆርጠው ያመጡትን እሸት ‹‹ና እንብላ›› አሏቸው፡፡ አባታችን ግን ‹‹ከየት እንዳመጣቸሁት ምንም ስለማላውቅ አልበላም›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ሀብተ ማርምን በቁጣ ዐይን እያዩአቸው ተቀምጠው ሲበሉ አባታችን ‹‹የማንችለው ዝናብ መጥቷልና ተነሡ በፍጥነት ወደቤታችን እንሂድ›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ‹‹ሰማዩ ብራ ነው ምንም ደመና የለውም፤ ነፋስም አይነፍስም፡፡ እኛ የማናየው አንተ ብቻ የምታየው ምን ነገር አለ?›› እያሉ በአባታችን ላይ ተዘባበቱባቸው፡፡ አባታችን ግን በጎቻቸውን እያስሮጡ በፍጥነት ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ወዲያውም በጣም ኃይለኛ ዝናብ ዘነበ፡፡ የጥፋት ውኃው በላያቸው እስኪፈጸምባቸው ድረስ እነዚያን እረኞች ከቦታቸው አልተነቃነቁም ነበርና በጥፋቱ ውኃ አለቁ፡፡ በዚያችም ሌሊት አቡነ ሀብተ ማርያን ከሰማይ ሦስት ጊዜ ‹‹ሀብተ ማርያም ሀብተ ማርያም›› የሚል ድምፅ ጠራቸው፡፡ አባታችንም እንደ ሳሙኤል ‹‹ጌታዬ ባሪያህ ይሰማሃል ተናገር›› ሲሉ ጌታችን አናገራቸው፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ለሚሰሙህ ለመረጥኳቸው ቃሌን ትነግራቸው ዘንድ ከእኔም ጋር በምሥጢር በባለሟልነት ትነጋገር ዘንድ መርጨሃለሁ›› አላቸው፡፡

➯ከጥቂት ቀንም በኋላ አባታችን በጎችን እየጠበቁ ሳሉ አንድ አመጸኛ መጣና በትራቸውን በኃይል ነጥቆ ወሰደባቸው፡፡ አቡነ ሐብተ ማርያምም ‹‹በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ እቋቋምህ ዘንድ ኃይል የለኝምና በትሬን መልስልኝ›› ቢሉት የትዕቢትን ቃል ተናገራቸው፡፡ አባታችንም ‹‹እምቢ ካልክስ እሺ የእግዚአብሔርን ኃይል ታያለህ›› አሉት፡፡ ወዲያም ያ አመጸኛ ላዩ ታች፣ ታቹ ላይ፣ ግራው ቀኝ፣ ቀኙ ግራ ሆኖ በአየር ላይ ተሰቅሎ ዋለና እየጮኸ አባታችንን ለመናቸው፡፡ አባታችንም ‹‹የቀጣህ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ›› ባሉት ጊዜ ከተሰቀለበት ወርዶ በእግሩ ቆመ፡፡ በዚያ የነበሩና ይህንን ተአምር ያዩ እረኞችም እጅግ ፈርተው ሄደው ለወላጆቻቸው ያዩትን ተናገሩ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ‹‹ቀድሞ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያለ ሲጸልይ ሲሰግድ አይተነዋል አሁንም ጠላቱን በነፋስ የሚቀጣ ይህ ልጅ ወደፊት ምን ይሆን!›› እያሉ አደቁ፡፡ ወላጆቻቸውም ይህን በሰሙ ጊዜ በግ ጠባቂነቱን አስተዋቸውና ወስደው ለመምህር ሰጧቸው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ በሚገባ ተማሩ፡፡

➯ከዚህም በኋላ አባታቸው ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች አንዷን እጮኛ አጨላቸው፡፡ ነገር ግን አቡነ ሀብተ ማርያም ‹‹አባቴ ሆይ እኔ ራሴን ለክርስቶስ በድንግልና ለመኖር አጭቻለሁ፣ ተራክቦዬም ቃለ ወንጌልን መስማት እንጂ ሌላ አይደለምና ለምን እንዲህ ትለኛለህ?›› አሉት፡፡ አባታቸውም ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ ያለ አቡነ ሀብተ ማርያም ፈቃድ ሙሽራይቱን ለማምጣት ሄደ፡፡ አባታችን ግን ሀገር ጥለው ለመሰደድ ከቤት ተደብቀው ወጡ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በመብረቅ አምሳል አባታቸውን ገስጻቸውና በዚህ ድንጋጤ ምክንያት ከዚህ ኃላፊ ዓለም ዐረፈ፡፡

➯አባታችንም የአባታቸውን ዕረፍት ሳያዩ አፋር ወደምትባል ሀገር ሄደው አባ ሳሙኤል ከሚባል ደግ መነኩሴ ቦታ ገብተው መነኩሴውን እያገለገሉት ኖሩ፡፡ አንድ ቀን አባታችን እንስራ ተሸክመው ውኃ ይቀዱ ዘንድ ወደ ወንዝ ወረዱና ውኃውን ቀድተው ሲመለሱ ድንጋይ አደናቀፋቸውና እንስራው ከላያቸው ላይ ወደቀ፡፡ ነገር ግን መሬት ከመድረሱ በፊት አባታችን ፈጥነው የጌታችን ስም በጠሩ ጊዜ እንስራው ወድቆ ሳይሰበር ተመልሶ በትከሻቸው ላይ ተቀመጠ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይከተሏቸው ነበርና ይህን ጽኑ ተዓምር አይተው እጅግ አደነቁ፡፡

➯እንዲሁ ከዕለታት በአንድ ቀን በሌሊት መብራት ለአባ ሳሙኤል እያበሩ ሳለ መብራቱ ከእጃቸው ላይ ወድቆ ጠፋ፡፡ መምህሩም አባ ሳሙኤል ቁጡ ነበረና ስለ መምህራቸው ቁጣ በጣም ደንግጠው ወድቆ የጠፋውነ መብራት ፈጥነው ባነሱት ጊዜ መብራቱ በእግዚአብሔር ተዓምር ራሱ በርቶ ታየ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን ተዓምራት አይቶ እጹብ እጹብ በማለት ‹‹የዚህ ቅዱስ ልጅ መጨረሻ ምን ይሆን?›› ብሎ ካደነቀ በኋላ ‹‹የዓለም ሁሉ የጥበብ መብራት ይሆናል›› ሲል ትንቢት ተናገረላቸው፡፡ እመቤታችን ለአባ ሳሙኤል ተገልጣላቸው የአቡነ ሀብተ ማርያምን ክብር ነግራዋለች፡፡ አባታችንም አባ ሳሙኤልን 12 ዓመት ከትሕትና ጋር እየታዘዙ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ኖረው ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተው ሄደው እለ አድባር በተባለ ገዳም መኖር ጀመሩ፡፡ ከቦታውም ደርሰው ጥቂት ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከአባ መልኬጼዴቅ እጅ የምንኩስናን ስርዓት ተቀበሉ፡፡ ይኸውም የሚዳው አቡነ መልኬጼዴቅ በደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉት ጻዲቅ ናቸው፡፡ ይህንንም የጻድቃኑን አባትና ልጅነታቸውን መሠረት በማድረግ የይሰበይ አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም ካህናት፣ መሪጌቶችና ዲያቆናት ግንቦት 4 ቀን ወደ ሚዳ መራቤቴ በመሄድ የአቡነ መልኬጼዴቅን በዓል እጅግ በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡

➯አቡነ ሀብተ ማርያምም ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ ገድላቸውንና ትሩፋታቸውን በማብዛት በሳምንት አንድ ጊዜ ቅጠልን ብቻ የሚመገቡ ሆኑ። አርባ አርባ ቀን ሰማንያ ሰማንያ ቀንም የሚጾሙበት ጊዜ ነበር። በሌሊትም ወደ ጥልቅ ባሕር እየገቡ መዝሙረ ዳዊት፣ አራቱን ወንጌላትና ሌሎች የጸሎት መጽሐፍትን ይደግሙ ነበር፡፡ ፊታቸውም እንደ ንጋት ምሥራቅ ኮከብ ያበራ ጀመር።

➯ከዚህም በኋላ ወደ ምሥራቅ ሄደው ጎሐርብ ወደምትባል ሀገር ደረሱ። በዚያም በዓት አጽንተው ሲጸልዩ ጌታችን ቅዱስ ገብርኤልንና ቅዱስ ሚካኤልን በቀኝና በግራ አስከትሎ ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን›› አላቸው። ያን ጊዜ አባታችን ከፈጣሪአቸው ግርማ የተነሳ ደንግጠው ከመሬት ወድቀው እንደ በድን ሆኑ። ጌታችንም አንስቶ ክቡራን በሆኑ እጆቹ አጸናቸውና ‹‹የመጣሁት ለጸናህ ነው ሰውነትህንም እንደ ንስር ላድሳት ነው እንጂ ላጠፋህ አይደለም፡፡ ድካምህና ገድልህ ሁሉ ለዘለዓለም መታሰቢያ ሊሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተጽፎልሃል ብዬ በእውነት እነግርሃለሁ። ለአንተ ለወደድኩህና ለመረጥኩህና ወዳጄ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ተጭነህ ወደምትሄድበት ቦታ የሚያደርስህ የብርሃን ሰረገላ ሰጥቼሃለሁ። እንደ አንተም ካሉ በዋሻ በመሬት ፍርኩታ ከሚኖሩ ከመረጥኳቸው ቅዱሳን ጋር ትገናኝ ዘንድ ወደ አራቱም አቅጣጫ ትበር ዘንድ የብርሃን ሠረገላ ሰጥቼሃልሁ። ዳግመኛም የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ትሄድ ዘንድ የእሳት ሠረገላ ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው። ዳግመኛም ‹‹በጸሎትህ አምኖ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ፣ ስምህን የጠራውን ዝክርህን ያዘከረውን ሁሉ የሀብተ ማርያም አምላክ ሆይ ከጠላት እጅ አድነኝ ያለኝን በኅሊና ያሰበውን በልቡናው የወሰነውን እፈጽምለታለሁ። አንተን ገድልህንና ቃል ኪዳንህን የናቀውን ያቃለለውን ሁሉ ፍጹም መበቀልን እበቀለዋለሁ። እንደ ወዳጄ እንደ ፊቅጦርም በእናቴ በማርያም ድንግል አተምኩህ›› ካላቸው በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ከእርሳቸው እንዳይለይ የዘወትር ጠባቂ አድርጎ ሰጣቸውና በታላቅ ግርማ ወደ ሰማይ ዐረገ።

➯አባታችንም ከጌታችን ይህን ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ነፍሳቸውን ‹‹ነፍሴ ሆይ ከፈጣሪሽ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት አፍ ለአፍ ትነጋገሪ ዘንድ ደፍረሻልና በጎም ሥራ ሳይኖርሽ ከፈጣሪሽ ቃልኪዳን ተቀብለሻልና ከዛሬ ጀምሮ እንደ መላእክት ዘወትር አትተኝ›› እያሉ ተጋድሏቸውን አብዝተው ቀጠሉ።......
September 1, 2026 25