🌅ኦርቶዶክሳዊ_የክርስትና_ሕይወት🌅: post #158 — TG.ME

🔥 🔥 #እሳቱን_እንቆስቁስ 🔥 🔥


አንዲት ሴት ነበረች። እንጀራ ልትጋግር እሳት አያይዛ ምጣዷን ጣደች። እዛው ኩሽናዋ ውስጥ ስትንጎዳጎድ ለአፍታ ቆይታ ወደ ምጣዷ ዘወር ብትል... አንድ ትልቅ አይጥ መኻል ምጣዱ ላይ ጉብ ብሎበት ተመለከተች። ነደዳት፤ ተበሳጨች። በእልኽ እሳቱን ልትቆሰቁስበት፣ ልታነደውም ያዘጋጀችውን ፍልጥ የአይጡን ወገብ ትልበት ዘንድ አነሣች። (የአይጡን ወገብ ስትሰብር የምጣዱ 'ወገብ' እንደሚሰበር ትዝም አላላት።) ፍልጡን በኹለት እጇ ጠበቅ አ'ርጋ ይዛ ወደ አይጡ በማነጣጠር ከአናቷ በላይ አንደረደረችው። ካንደረደረችበት ወደ ፊት ከመሰንዘሯ በፊት ግን ነገሩን ኹሉ በሽንቁር አጮልቃ ስትከታተል የቆየችው ጎረቤቷ "እቴ! ፍልጡን ተይው! እሳቱን ቆስቁሺው" አለቻት። (እሳቱ ሲያቃጥለው በራሱ ይሔዳል በሚል እሳቤ)።
...
#ምጣድ_የተባለ_ሰውነታችን_ነው_ሰብእናችን። #እሳት_የተባለች_ሃይማኖት_ናት_ተዋሕዶ። "እሳተ አምጻእኩ ለብሔር" እንዲል። (ሉቃ. 12:49)።
ምጣድ የተባለ ሰውነታችንን እሳት በተባለች ሃይማኖት ላይ ስንጥድ ኹሌም ቢሆን አይጡ ይመጣል። ካለ ምንም ኃፍረት መኻል ምጣዳችን ላይ ጉብ ይላል።

#ዘረኝነት_አይጥ_ነው_ድንገት_ሳናስበው_በጣድነው_ምጣድ_ላይ_ጉብ_የሚል። ሰማያዊም ምድራዊም እንጀራን ለማብሰል የሚያስችል ግለት ሳይኖረን የሚሰፍርብን ጥቁር አይጥ። በመንፈሳዊነት ዋዕይ ካላቃጠልነው ሊቦጠቡጠን የተጫነን ሸክም። #አይጥ_ልብስን_ይቀዳል_በአንድነት_የተሰፋውን_ይለያያል_ዘረኝነትም_እንዲሁ_ነው_ሰብእናን_ይቀዳል፤ በአንዲት ሃይማኖት የአንድ አካል ብልት የሆንነውን ይለያያል።

#ተሐድሶ_አይጥ_ነው_ምንፍቅና_ከተባለው_የአይጥ_ዝርያ_የተገኘና_በክሕደት_የሰባ_ጠብደል_አይጥ። እሳቱን ቶሎ ቆስቁሰን ምጣዳችንን አግለን ተለብልቦ ካልሔደ አደገኛና መርዛማ ነው፤ በ'ኩሱ' እንኳን ምጣዳችንን ለመበከል ወደ ኋላ የማይል ነውረኛ አይጥ ነው። ከቻለ ምጣዳችን እንዲሰበር ካልቻለ ደግሞ እንዲሰነጠቅ የማያደርገው ጥረት የለም። መዝሙር በሚመስል ዘፈን፣ ሽብሸባ በሚመስል ዝላይ ምጣዳችንን በማወዛወዝ ዱቄት ሊያደርግ የሚጥርና ተመስጦን የሚረብሽ አይጥ ነው። ያሰስነው ምጣድ ላይ ተቀምጦ እኛን በማበሳጨት ፍልጡን እንድናነሣ ዘወትር ይጋብዘናል፤ ዋና ዓላማው የምጣዱ መሰበር ነዋ!

ዋናዎቹን አነሣን እንጂ እሳቱ ላይ ስንጣድ የሚወጡብን አይጦች ብዙ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ወዳጆቻችንም አይጥ ሆነው ይመጣሉ። ቤታችን ሽንቁር እስካለው ድረስ ብዙ የአይጥ ዝርያዎች ምጣዱ ላይ ለመውጣት መሽቀዳደማቸው አይቀርም።

በዚህን ጊዜ ታዲያ እሳቱን በመቆስቆስ ፈንታ ፍልጡን ካነሣን የአይጦቹን ዓላማ አሳካን ማለት ነው።

#በሃይማኖት_ፍቅር_ልቡ_የነደደ_ስንቱ_አይጡን_ለማባረር_ፍልጡን_አዘውትሮ_እያነሣ_ስንት_ምጣድ_ሰበረ!

ወዳጄ ሆይ! አይጡ ተቃጥሎ እንዲሔድ እሳቱን ቆስቁሰው 'ባክህ። #ጸሎት_መቆስቆሻው_ነው_ጾም_ስግደት_ትምህርት_ቅዳሴ_ጉባኤ_ንስሐ_ቁርባን_ሱባኤ_ምጽዋት_ምግባር_ኹሉ_መቆስቆሻዎች_ናቸው።

ይህ ማለት ግን በሰበቡ ተዘናጋ ማለት አይደለም። ዋና ዓላማህ እንጀራ የሚገኝብህ ምጣድ መኾን ነው። መቼስ አይጥ ባለበት ምጣድ እንጀራ እንደማይጋገር ግልጽ ነው። ስለዚህ እንጀራን ለማግኘት አይጡ መሔድ አለበት። መጀመሪያ አይጥ መሆኑን አረጋግጥ፤ ከዚያም አባረው!

ግን አባራለው ብለኽ ምጣዱን እንዳትሰብር ተጠንቀቅ፤ እሳቱ መንደዱን አረጋግጥ፤ በርትተህ ቆስቁስ...

የኔና ያንተ ትልቁ ችግር ለመቆስቆስ አዋጅ መጠበቃችን ነው። "እነ እንትና ለምን ለ3 ቀን ቆስቁሱ የሚል አዋጅ አያውጁም?" እንላለን። "አትቆስቁሱ" እንዳላሉ እንዘነጋለን። ላለመቆስቆስ ሰበባችን ብዛቱ! ታዲያ ምጣዱ እንዴት አይቀዘቅዝ!? ባልጋለው ምጣዳችን ላይስ አይጦቹ እንዴት አይፈነጩበት!?

ወዳጄ ሆይ!
#ለምጣዳችን_ደኅንነት_እሳቱን_እንቆስቁስ!

✍ ዲ/ን ሕሊና በለጠ

🔥🔥 @SPIRITUALITY 🔥🔥
🔥🔥 @SPIRITUALITY 🔥🔥
June 22, 2019 9.3K 84