✝መጽሐፍን በመመርመር ተወስነህ እንድትኖር ዕወቅ በዚያውም ጸንተህ እንድትኖር ዕወቅ ይህን ያደረግህ እንደሆነ ራስህን ታድናለህ´´✝
📚📚📚 📚📚📚
📙መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክታት መካከል ለግል ሰዎች የተላኩ መልእክታትም ይጠቃለላሉ። ከእነዚህም ወደ ጢሞቴዎስ የላካቸው ሁለቱ መልእክታት በኤጲስ ቆጶስነት ሲያገለግል ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ የሚያስገነዝቡ ናቸው። በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ሊኖር የሚገባውን ትክክለኛ ሥርዓት ከዘረዘረ በኋላ የሕዝቡ መሪ ሆኖ የተሾመው ራሱ ጢሞቴዎስ በሕዋሳቱ ላይ ሊሠራ የሚገባውን ሥርዓት አያይዞ ይጽፍለታል። ከእነዚሀ ምክሮች መካከል ከላይ በርእሳችን የጠቀስነው ኃይለ ቃል አንዱና ዋነኛው ነው። ቃሉ ሁልጊዜ መጻሕፍትን በመመልከት መኖር እንደሚገባ ይህን ማድረግም ያለውን በረከትም ይገልፃል። «ራስህንና የሚሰሙህን ታድናለህ» በማለት። ይህም መጻሕፍትን መመልከት የመዳንና ያለመዳን (የህልውና) ጉዳይ መሆኑን ያሳየናል። ነቢዩ በትንቢቱ «ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል» ያለውን ቃል ጌታ በወንጌል «ስኅትክሙ በኢያእምሮ መጻሕፍት» «መጻሕፍትን ባለማወቅ ሳታችሁ።» ብሎ ምክንያቱን ከመጻሕፍት ጋር ማገናኘቱ እውነትም መጻሕፍትን ካለማንበብ ስኅተት ሲብስም ጥፋት የሚመጣ መሆኑን ያስተምረናል። ሐዋርያው ደግሞ የጉዳዩን ታላቅነት በሚያስረዳ መልኩ «ወዘልፈ ሀሉ ባቲ» «ሁልጊዜ በእርሱ ኑር» በማለት መጻሕፍትን መመልከት የጥቂት ጊዜያት ሥራ አለመሆኑን አያይዞ ገልጿል።
📚📚📚 📚📚📚
📘በሁለተኛው መልእክቱ ላይ ደግሞ «ተአምር በኀበ መኑ ተምህርከ እምንዕስከ መጽሐፈ ቅዱሰ በሃይማኖተ ኢየሱስ ክርስቶስ» «ከሕፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማን እንደተማርክ ታውቃለህና» በማለት በመጀመሪያው መልእክቱ ላይ የጠቀሳቸውን ትእዛዛት የበለጠ አብራርቷቸዋል። ሁልጊዜ አንብብ ብሎ ያዘዛቸው መጻሕፍት ከመጻሕፍተ ጥንቆላ የተለዩ ንጹሐት ከመጻሕፍተ ምኑናት የተለዩ ክቡራት እንደሆኑ ለማሳየት «ቅዱሳት መጻሕፍት» ብሎ ሲጠራቸው እነዚህም ልብ እንደፈቀደ የሚነበቡ ብቻ ሳይሆኑ የምንማራቸው መሆኑን ለማሳየት «እንደተማርከው» የሚል ቃልን አስቀምጦልናል። መማሩም ከሐሰተኛ መምህር እንደሆነ «ዕውርን ዕውር ቢመራው» ይሉት ብሂል ይፈፀማልና «ከእኔ እንደተማርከው ታውቃለህና» በማለት ለገበታ ሰው እንዲመርጡ ለትምህርትም (ለመፅሐፍትም) መምህር መምረጥ እንደሚገባ ተናግሯል።
📚📚📚 📚📚📚
📗ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በትእዛዝ ደረጃ ብቻ የተገለፁ ሳይሆኑ በቅዱሳንና በቅዱሳን አምላክ በጌታ ሕይወት ውስጥ የተገለጡ እውነታዎች ናቸው። በቅዱስ መጽሐፍ ላይ ጌታችን ወደ ምኩራብ ገብቶ የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ ገልጦ እንዳነበበ ተጽፏል። ስለ ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ታሪክ የተፃፈባቸው መጻሕፍትም እመቤታችን ቅዱሳት መጻሕፍትን ታነብ እንደነበር በተለይም «ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች» ከሚለው ክፍለ ትንቢት ስትደርስ «በዘመኗ ደርሼ ምነው ባገልገልኳት» እያለች ትመኝ እንደ ነበር ይተርካሉ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ደስ ይበልሽ» እያለ ሲያበሥራት ከመዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ›› ‹‹እንዲህ ያለ ሰላምታን እንዴት ይቀበሉታል?›› ብላ መናገሯ እናቷ ሔዋን የሳተችበትን ታሪክ ከኦሪት መጻሕፍት መማሯን ያሳያል። በእነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በእነ ቅዱስ ቄርሎስ በገዳማት ብቻቸውን ተጥለው ባሉ በቅዱሳን ዘንድ መጻሕፍት የነበራቸውን ታላቅነት «እንዳንተርክ ጊዜ ያጥርብናል።»
📚📚📚 📚📚📚
📕በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ታዋቂነትን ያገኙ ሰዎች፣ ታላላቅ መሪዎችና ርቱዕ አንደበት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሰዎች በእርግጠኝነት አንድ የጋራ ነገር አላቸው ይህም ምንም እንኳን ምኑናት ቢሆኑም መጻሕፍትን ማንበባቸው ነው። መጻሕፍትን ማንበብ ነፍስን ለማዳን ለሌላውም የሕይወት መንገድ ከመሆንም ሌላ ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ ለመመልከትና አእምሮንም ለማስፋት ይረዳሉ። የመጻሕፍትን ጥቅም ለመናገር እጅግ ብዙ መጻሕፍትን ብንጽፍ እንኳ ሁሉን ዘርዝረን አንዘልቀውም። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ቋንቋና ጽሑፍ ያላቸው እንደመሆናቸውና አንባቢያን የሆኑ ሊቃውንት በፊታቸው እንደ አብነት ሳሉላቸው በንባብ የሰነፉ መሆናቸው ምንም ዓይነት ምክንያት ሊሰጠው አይችልም።
📚📚📚 📚📚📚
📒ስለዚህም እንደ ጢሞቴዎስ «ከሕፃንነትህ ጀምረህ» የሚለው ምስክርነት ባይሰጠንም እንኳ ለራሳችን ሕይወትና ሌሎቹንም ማዳን የሚገኝበትን ጥበብ የሚያስተምሩትን ቅዱሳት መጻሕፍት እናንብብ ከእውነተኛ መምህራን እንማር! «የተፃፈው ሁሉ እኛን ለመምከር ተፅፏል።» ተብሎ ተጽፏልና። ሮሜ 15፥3
📖ወስበሐት ለእግዚአብሔር!📖
May 31, 2019 4.3K 28