#አዲስ_ዓመት
#New_Year
መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናንብብ? ጠቃሚ መርሆች
ክፍል-5
(የመጨረሻ ክፍል)
#ትንቢቶች- የትንቢት መጻሕፍት ስለወደፊቱ ሁኔታዎች የሚናገሩ ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በምንተረጉበት ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው ከሚገቡ ክፍሎች መካከል ትንቢቶች የመጀመርያዎቹ ናቸው፡፡ የሚከተሉት ጥያቄዎች የትንቢት መጽሐፍትን ለመረዳት ያግዛሉ፡-
👉የቋንቋ አጠቃቀሙ ምን ዓይነት ነው? (ትዕምርታዊ፣ ቅኔያዊ፣ ራዕያዊ፣ አቡቀለምሲሳዊ፥ ወዘተ.)
👉የምንባብ አውዱ ምንድነው?
👉የትንቢቱና የተናጋሪው ታሪካዊ ዳራ ምንድነው?
👉የተሰጠው ተስፋ አኳኋናዊ (conditional) ነው ወይንስ ኢ-አኳኋናዊ (unconditional)?
👉የተነገረው ትንቢት የተፈፀመ፣ እየተፈፀመ ያለ ወይንስ ወደፊት የሚፈፀም?
#ምሳሌዎች- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶቹን ብዙ ጊዜ በምሳሌዎች ያስተምር ነበር፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች ትምህርቶቹን ይበልጥ ያብራራሉ ወይንም ደግሞ ከሰዎች አዕምሮ እንዳይጠፉ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች በምናነብበት ሰዓት ከእነርሱ በፊት ወይንም በኋላ የተነገሩትን ነገሮች ልብ ብሎ ማንበብ አስፈላጊ ነው፡፡ የምሳሌ እያንዳንዱ ነጥብ ትርጉም ባለው መልኩ ከፍቺው ጋር ላይገናኝ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ስለ ወይን እርሻ ገበሬዎች በተሰጠው ምሳሌ ውስጥ ከተዘረዘሩ የወይኑ ጌታ ባህርያት መካከል ከእግዚአብሔር ባሕርት ጋር የማይገጥሙ አሉ (ማቴዎስ 21፡33-43)፡፡ ምሳሌዎች ደግሞ በክፍሉ ላይ ከተጠቀሰው ፍቺ ውጪ ሌላ የተደበቀ ትርጉም ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፤ ስለዚህ በወቅቱ ምሳሌው የተነገረበትን ትክክለኛ ነጥብ ካገኘን ዘንዳ ሌላ አላስፈላጊ ሐተታ ውስጥ መግባት አያሻንም፡፡
#መልዕክቶች- መልዕክቶች እንደስማቸው ከሰዎች ወደ ሌሎች የተላኩ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ደብዳቤዎች ተራ ደብዳቤዎች ሳይሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፏቸው ናቸው፡፡ የእነዚህን መልዕክቶች አጻጻፍ በምናይበት ጊዜ በአብዛኛው ተመሳሳይ የሆነ ቅርፅ እንዳላቸው እናስተውላለን፡፡ እነዚህም፡-
👉ጸሐፊው
👉የተቀባዩ ስም
👉ሰላምታ
👉ጸሎት፣ መልካም ምኞት ወይንም ምስጋና
👉የመልዕክቱ ዋና አካል
👉የመጨረሻ የስንብት ሰላምታ ናቸው፡፡
መልዕክቶችን በምንተረጉምበት ሰዓት ታሪካዊና ምንባባዊ አውዳቸውን ተከትለን የማጥናት መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪም መልዕክቶች እንደመሆናቸው ሳናቆራርጥ የንባብ ሂደቱን መጨረስ ይገባናል፡፡
3. ማዛመድ
ዕብራውያን 4፡2 ላይ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም” ይላል፡፡ ያጠናነው ቃል ከሕይወታችን ጋር ካልተዛመደ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን መንገዶች ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን ብንመረምር ለአዕምሯችን ዕውቀትን ከማግኘት ያለፈ ለመንፈሳችን የሚሆን በረከት ልናገኝ አንችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዘመናት በፊት ለነበሩ ሰዎች የተሰጠ ቃል ነው፤ ነገርግን በሐቲትና በመተርጎም በእኛና በእነርሱ መካከል የሚገኙትን የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባሕል፣ የታሪክ፣ የቦታ፣ የአጻጻፍ፣ የዘመን፣ ወዘተ... ልዩነቶችን አስወግደን በየትኛውም ዘመንና በሁሉም ቦታ ሊሠራ የሚችል ለሁሉም ሕዝቦች ጠቃሚ የሆነን መልዕክት እናገኛለን፡፡ ማዛመድ ማለት በአጭር ቋንቋ ያጠናነው ቃል አሁን ስላለንበት ሁኔታ ወይንም ደግሞ ስለ ሕይወታችን ምን እንደሚልና ቃሉን ተግባራዊ ማድርግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በማወቅ በቃሉ መሠረት መኖር ማለት ነው፡፡ ዕለት ዕለት ይህንን ማድረግ ከቻልን የእግዚአብሔርን ኃይልና አብሮነት በሕይወታችን ውስጥ እንለማመዳለን፡፡
ይህንን ጽሑፍ ስንደመድም አፅንዖት ሰጥተን ልንናገረው የምንፈልገው የመጨረሻው ነጥብ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የመንፈስ ቅዱስን ድርሻ ልንዘነጋ እንደማይገባን ነው፡፡ እርሱ ከማንኛውም መዝገበ ቃላት፣ ሐተታ ወይንም ደግሞ አስተማሪ ይልቅ ሊያስተምረን የሚችል ሕልውናው እውን የሆነ መምህር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራን ነግሮናል (ዮሐንስ 16፡13)፡፡ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ቅዱሳት መጻሕፍትን ያልተማሩ ሰዎች ቢሆኑም እንኳ መንፈስ ቅዱስ እራሱ ስላስተማራቸው ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የነበራቸው ጥልቅ ዕውቀት በወቅቱ የነበሩትን የአይሁድ መምህራን ሳይቀር አስገርሞ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 3፡13)፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናነብ እኔና እናንተንም መንፈስ ቅዱስ እንዲያስተምረን በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል፡፡
“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14፡26)
ምንጭ:- www.ewnetlehulu.org
ወደ ቻናሉ ለመ🀄️ላ🀄️ል፦ @Holy_scriptures
2August 26, 2026 393 4