ሕዳር መጨረሻ 2014 ዓመተ ምኅረት በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ደሴ ገባሁ። የዚያን'ለት ደሴ ግራ የተጋባች… — Tamene Mengste Wube — TG.ME

ሕዳር መጨረሻ 2014 ዓመተ ምኅረት በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ደሴ ገባሁ።

የዚያን'ለት ደሴ ግራ የተጋባች ከተማ ነበረች።ለ40 ቀናት በሕወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ሥር ሰንብታ ገና እኛ የገባን'ለት ወደ መደበኛ ሕይወት መመለሷ ነው።

ላይኛው አንቀጽ ፖለቲካ ነው።

እነሆ ውበትን ፍለጋ በጥምዙ እና ጠባቡ የደሴ መንገድ ወደ ቧንቧ ውሃ ሰፈር እንጓዝ።

በዚህ ሁሉ ጉዞ ሂደት ያ—የጸሐፊ ብዕር ያስጨረሰ፣የባለቅኔ ምናብ ያሟጠጠ፣የዘፋኝ ጉሮሮ የቧጠጠ፣የተመልካች ቀልብ የበጠበጠ የወሎ ሴት ልጆች ውበት የለም።

አንዲትም ቆንጅዬ—ወሎዬ ዕያዬሁ አይደለም።

ቧንቧ ውሃ ደረስን።በቀኝ በኩል «Time» የሚባል ሆቴል ደብሮት ቆሟል።

እዚህ ሥር ግን ትክክለኛዋ የወሎ ቆንጆ ከትንሽ እህቷ ጋር ቁጭ ብላ ለወራት የሆነውን፣ዛሬ እየሆነ ያለውን እና ነገ የሚሆነውን ታሰላስላለች።

ተያዬን።

ብርቅ ሆነችብኝ።ብቻዋን የወሎን ልጆች ቁንጅና ልታስመሰክር በዚያ የከተማ ምድረ በዳ የተከሰተች የውበት እርግብ መሰለችኝ።

እየፈራሁ—እየተባሁ ወግ አስጀመርኳት።

ከ40 ቀን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግቢ መውጣቷን ነገረችኝ።እኛ ብርቅ እንደሆንባትም አጫወተችኝ።

በጠይም ፊቷ ውስጥ የተከማቸው ደም የውበት ቅመም ይመሥለኝ ጀመር።እዚያው ሥለቁንጅናዋ እያሰብኩ ስሟሟ ትዝ ይለኛል።

ምን ያረጋል🙁?

እነ መንጌ በጦርነት መሐል እንዲህ እንድመሰጥ አይፈቅዱልኝም።ወዲያው አጣድፈው ከወሎዋ አበባ ለዩኝ።እሷም ከርቀት ዕያየችን እጆቿን አውለበለበች።

ከዚያች ቀን በኋላ ደሴ ውስጥ ለአምስት ወራት ኖሬዐለሁ።ከጦርነቱ በኋላም ሁለት ጊዜ ተመላልሸ አለሁ።

ግን ያችን ለመጀመሪያ ጊዜ የወሎ ልጆችን ውበት በአካል ያዬሁባትን እንቁ ደግሜ ለማግኘት አልታደልኩም።

እዚህ የሚታዩት የወሎ ቆነጃጅት ልጆች በይሁኔ በላይ ሰሞነኛ «ዞማዬ» ቪዲዮ ውስጥ ያሉ ናቸው።
August 27, 2026 168