አንዳንድ ሰው አለ - - -🗣 የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው መክሊት አለው። አንዳንድ ሰው ገና… — 𝐅𝐢𝐧𝐟𝐢𝐧𝐧𝐞𝐞 𝐏𝐫𝐞𝐬𝐬 — TG.ME

🚨 አንዳንድ ሰው አለ - - -🗣

የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው መክሊት አለው። አንዳንድ ሰው ገና በማለዳ/በልጅነት መክሊቱን አግኝቶ፤ የተሰጠውን መክሊት ይዞ እንደ አብሪ ኮኮብ ለብዙሃን እያበራ እስክ ህይወቱ ፍጻሜ ይዞ የሚዘልቅ። የተሰጠው መክሊት ሳይበርዝና ሳይከልስ፣ ሳያልከስከስና ለጊዜያዊ ጥቅም ለድርድርና ለሽያጭ ሳያቀርብ፣ አክብሮና ተከብሮ፣ ለሙያው ሥነ ምግባር ዘብ ቆሞ፤ ከዘመን ዘመን፣ ከትውልድ ትውልድ አገዛዝ ቢወጣ ቢውርድ፣ ውሎ ባደረ ቁጥር እንደ ወርቅ ደምቆ፣ እንደ ጠጅ ጣፍጦ፤ በሰብዕናውና በሙያው የሰው ልኬት የሚሆነው አለ አንዳንድ ሰው!!

የብዙሃን እናት፣ የእናቶች ተምሳሌት፣ የእልፍ ታጋዮች ጽናት፣ እልፍነሽ ቀኖ አንዱዋ ናት። ሰው እንዴት ዕድሜ ልኩን በሁሉም ዕድሜና ጾታ፣ ከትውልድ እስክ ትውልድ አስጨፍሮም አስለቅሶም፣ በትግልም በትዳርም አጀግኖና አዋህዶ፣ እንደ እንስት በጥዑም ዜማና ግጥም፣ እንደ ወንድ በጌረርሳ፣ እንደ ወታደር በጦር ሜዳ፣ እንደ እናት ወልዶ መሳም፣ እንደ ሽማግሌ አስታራቂና መካሪ፣ እንደ ወንጀለኛ ግዞተኛ፣ ታላቅ አገርና ህዝብ እያላት ስደተኛ፣ ፍልቅልቅ ቀልደኛ፣ ሆደ ቡቡ ሀዘንተኛ፣ ለወገን መከታ፣ ለአገዛዝ ራስ ምታት፣ ከትንሽ እስክ ትልቅ አክብራና ተከብራ፣ የሰው መመዘኛ ልኬት ሆና በሥጋ ተለየችን፣ እልፍ ትውስታና ትዝታ አሳቅፋ አለፋች እልፍነሽ ቀኖ ኬኛ😢

አንዳንድ ሰው ደግሞ አለ። መክሊቱን ሳያውቅና ሳያገኝ ሲቅበዘበዝ፣ በታሪክ አጋጣሚ እጁ በገባ ሥልጣንና ገንዘብ፣ መከራ አምጦ ሰቆቃ የሚያዋልድ፣ ቂም በቀል ቋጥሮ፣ ህዝብ ከህዝብ የሚያፋጅ፣ በእብሪት ተስቅሎ፣ በውርድት የሚተንፍስ፣ በበታችነት ስሜት እንደ እልፍነሽ ቀኖ ሙሉ ሰው ለማዋረድ ግዞት ቤት የሚወረውር፣ የሴት ልጅ ጽጉርን በደርቅ የሚላጭ፣ ደብድቦና አሳዶ የማይረካ፣ ሥልጣንና ንዋይ አላፊና ጠፊ መሆኑን ዘንግቶ፤ በአጭብጫቢና አጃቢ ሙገሳ፣ ሰማይን በእርግጫ ካላልኩ እያለ ስንጠራራ ጊዜ በካልቾ ብሎ ታሪኩ የሚያበቃ። ከዚህ የማይማር ባለተራ ቢፈራረቅ የአንዲት እልፍነሽ ቀኖ የሩብ ሩብ ልኬት የማይሞላ፤ አለ አንዳንድ ሰው - - -

ብቻ እንደ እልፍነሽ ቀኖ ጅማሮና ፍጻሚያችሁን ያሳምርልን እየተባባልን የምርቃት ሞዴል እናድርጋት። ሥምን መላዕክ ያወጣዋል እንዲሉ አንድ ሆና እልፍ ሆና የኖረችና ወደፊትም የምትኖር የሙያና የሰው ውሃ ልክ፤ እንደ ተወደደች እንደ ተከበረች፣ የትግሉዋን ውጤት በጥቂቱም ቢሆን ፍሬዋን ያየች፣ ቀሪውን በእልፍ ልጆቹዋ ግቡን እንደሚመታ አምና ያሳመነች ነፍሶዋ እረፍት ያገኘች፤ ከህሊና ፅጽት የጽዳች፣ መክሊቱዋን በሰላሳ፣ ስልሳና መቶ እጥፍ ያበዛች፤ እንዳንቺ ዓይነቱን ያብዛልን የኦሮሞ አምላክ🙏🙏

ጊፍቲ ኪያ💔
❤2
September 6, 2026 374 2