የጽናት ቀን መከበሩ ሀገራዊ አደራን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተገለፀ። የኢፌዴሪ… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME

የጽናት ቀን መከበሩ ሀገራዊ  አደራን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ  ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተገለፀ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 03 ቀን 2018 ዓ.ም

የጽናት ቀን መከበሩ የቀድሞ ትውልድ ለሀገሩ ያሳየውን ጽናት፣ የሀገር ፍቅር፣ አገልግሎት፣ ተሞክሮና መስዋዕትነት ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍ የትውልድ ቅብብሎሽ መድረክ መሆኑ ተገለፀ።

በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተከበረው በዓል ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ እና አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ ፣ የጽናት ቀን ትውልዱ ከአባቶቹ የሀገር ፍቅር፣ የአንድነትና የጽናት እሴቶችን የሚማርበት መድረክ ነው ብለዋል።

የቀድሞው ትውልድ በሀገር ፍቅሩና አገልግሎቱ ያከማቸው ልምድና እሴት በትውልድ ቅብብሎሽ ለቀጣዩ ትውልድ መሻገር እንዳለበት የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ ፣ ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ክብር፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር የሀገር አደራውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ በተለይ ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት የሚተጋውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአገልግሎት ታሪክ ከቀድሞው ትውልድ ወደ አሁኑ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለውን ሚና የሚያጎላ መሆኑም ገልፀው፣ ሠራዊቱ የቀድሞውን ትውልድ የሀገር ጥበቃ ተልዕኮ በመረከብ በተለያዩ ዘመናት ሀገርን በማገልገል የቀጠለ ተቋም በመሆኑ፣ የጽናትና የሀገር አገልግሎት እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፉ የትውልድ ቅብብሎሹን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት አስር አለቃ ፎዚያ ሙሳ እና ወታደር ቃልኪዳን ደሴ የተባሉ የሰራዊቱ አባላት፣ በዝግጅቱ መሳተፋቸው ከቀድሞ ትውልድ የሀገር አገልግሎት ተሞክሮ ለመማር ዕድል እንደሰጣቸው ገልፀው፣ በተሰለፉበት የሥራ መስክ ሀገራቸውን በጽናትና በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውና ለሚሰጣቸው ቀጣይ ግዳጅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የዝግጅቱ ታዳሚዎች አቶ ዮሐንስ ገናሌ፣ አቶ ማርቆስ ገዛኸኝ እና ተማሪ ነብያት ነብዩ በበኩላቸው፣ የጽናት ቀን  በዓመት አንድ ቀን ብቻ የሚዘከር ሳይሆን በየዕለቱ በተግባር ሊገለጽ የሚገባ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።

ዝግጅቱ ለመከላከያ ሠራዊቱና ለጸጥታ አካላት ያለውን ክብርና አድናቆት ለመግለፅ፣ ለሀገር ሰላምና ደህንነት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለትውልዱ ለማስተዋወቅ እና የሀገር ፍቅርን ለማጠናከር ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተሳታፊዎቹ  ሀገራዊ አንድነትን ከሚያዳክሙ ከፋፋይ አስተሳሰቦችና የተሳሳቱ ትርክቶች በመራቅ፣ የሀገርን ሰላም፣ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ማጠናከር የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል። ለሀገር ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት የሚተጉ የመከላከያ ሠራዊትንና የጸጥታ አካላትን ማክበርና ማመስገንም የሀገር ፍቅርና የዜግነት ኃላፊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

 ሀገራዊ አንድነትን ሊያዳክሙ ከሚችሉ ከፋፋይ ሀሳቦችና ከተሳሳቱ ትርክቶች በመራቅ፣ የሀገርን ሰላምና አንድነት ማጠናከር የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች፣ የጸጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አመራርና አባላት፣ አባት አርበኞች እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ ብዙአየሁ ተሾመ
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/

https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0

https://www.facebook.com/fdredefense.official
❤16👍8🔥2
September 8, 2026 2.9K 1
የጽናት ቀን መከበሩ ሀገራዊ አደራን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተገለፀ። የኢፌዴሪ… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME