የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በዌብ ልማት ቴክኖሎጂ አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን፣ በተማሪወች… — Dire-Dawa University — TG.ME

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በዌብ ልማት ቴክኖሎጂ አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን፣ በተማሪወች የተሰሩ 12 አዳዲስ የዌብሳይት ፕሮጀክቶችም ይፋ ሆነዋል

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (DDU IoT) ከSTEM Synergy ጋር በመተባበር ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያዘጋጀውን የ45 ቀናት የክረምት ወራት የዌብ ልማት (Web Development) እና ኮዲንግ ስልጠና በደማቅ የምረቃ እና የሰርተፍኬት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት በስኬት አጠናቋል።

ከተለያዩ የድሬዳዋ አስተዳደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተመረጡት እነዚህ ተማሪዎች፡ በቆይታቸው በHTML, CSS, JavaScript, PHP እና MySQL መሰረታዊ እና ተግባራዊ የኮዲንግ እውቀቶችን የቀሰሙ ሲሆን፤ በስልጠናው መጨረሻም ማህበረሰባዊ እና ተቋማዊ ችግሮችን መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ 12 የፈጠራ የዌብሳይት ፕሮጀክቶችን ማልማት ችለዋል።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ካሲም፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ፣ እና የSTEM Synergy የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዮት ላቀው ለተመረቁት ሰልጣኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

እንግዶቹ በመልእክታቸውም፡ ወጣቶችን ገና በለጋ እድሜያቸው ለሀገራችን የዲጂታል መፃኢ እድልና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ማዘጋጀት ተካኪ የሌለው ሚና እንዳለው ገልጸው፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማስገባት መሰረታዊ የኮዲንግ እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ ተቋሙ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን መሆን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
❤9🖕2
September 8, 2026 2.4K 5
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በዌብ ልማት ቴክኖሎጂ አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን፣ በተማሪወች… — Dire-Dawa University — TG.ME