የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበዳሪዎች ቻናል Development bank of Ethiopia borrowers channel: post #116 — TG.ME

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባዘጋጀው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም በይፋ በተከፈተው ፎረም ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የፋይናንስ ተቋማትን ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በፎረሙ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ መሬት በወረደ አጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያለው የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል እድገት ሳያስመዘግብ መቆየቱን ያነሱት ፕሮዚዳንቱ በዘርፉ የተጋረጡ መሰናክሎችን ለማለፍ አካታችና ዘመኑን የዋጀ ሥርዓት ለመፍጠር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን አመላክተዋል። የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው በ12 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስት ብድር ወደ ዜሮ መውረዱን በመግለጽ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንደ ዋጋ ንረትና የውጪ ምንዛሬ እጥረት ባሉ በርካታ ችግሮች ሲፈተን እንደነበር አስታውሰው ችግሮቹን ለመፍታት ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷንና በዚህም የውጪ ምንዛሬ እጥረትን መፍታት እንደተቻለ እና የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ የፋይናንስ ዘርፍ እውን መደረጉን አብራርተዋል፡፡ በፎረሙ የመጀመሪያ ቀን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፍ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ/ር እመቤት መለሰ አጠቃላይ የፋይናንስ ሴክተርን በተመለከተ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ፓናሊስት በመሆን ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ ዝርዝሩን የምንመለስበት ይሆናል፡፡

May 15, 2025 712 1 1