#ቅዱስ_ለውንትዮስ (ስንክሳር)
➯በዚህችም ቀን ቅዱስ ለውንትዮስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ክርስቲያን ከሀድያን ከሆኑ ሠራዊት ጋር ይኖር ነበር ሀገሩም ጠራብሎስ ነው መልኩም ያማረ በገድሉም ፍጹም የሆነ ነበር። አምላክ ያስጻፋቸው መጻሕፍትንም ያነብ ነበር።ይልቁንም የዳዊትን መዝሙር ሁልጊዜ ያነብ ነበር። ባልንጀሮቹ ለሆኑ ወታደሮችም ያስተምራቸው ይመክራቸውም ነበር።እግዚአብሔርንም እንዲፈሩ ያስገነዝባቸው ነበር። የማይጠቅሙ የረከሱ የአማልክትንም ሸክም ከትከሻችሁ ጣሉ ይላቸው ነበር። ከስሕተትም ተመልሰው ክብር ይግባውና በጌታችን ያመኑ አሉ። ከእነርሱም ወደ መኰንኑ ሒደው ለውንትዮስ አማልክትን አቃለላቸው ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ ነው ይላል ብለው የከሰሱት አሉ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀርቦ ጠየቀው እርሱ ግን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስን እንደሚያመልከው በመኰንኑ ፊት ታመነ ጳውሎስ ከፈጣሪዬ ከክርስቶስ ማን ይለየኛል እንዳለ ከታናሽነቴ ጀምሮ በፍጹም ልቡናዬ አመልከዋሁ ለእርሱም እሰግዳለሁ አለው። መኰንኑም እጆቹንና እግሮቹን አሥረው በወህኒ ቤት ውስጥ እንዲጥሉት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት። በማግሥቱም መኰንኑ አቅርቦ እንዲህ አለው በምን ኃይል የንጉሥን ትእዛዝ ደፍረህ ትተላለፋለህ ሰዎችንም አማልክትን ከማምለክ በምን ኃይል ትመልሳቸዋለህ ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። በእውነት ሰዎች ሁሉ ክብር ይግባውና ወደጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት እንዲገቡ እኔ እሻለሁ አንተም ስሕተትህን ትተህ ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስን ብታመልከው የረከሱ አማልክትንም ማምለክ ብትተው የዘለዓለም መንግሥትን በወረስህ ነበር።
➯ይህንንም በሰማ ጊዜ መኰንኑ እጅግ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስኪፈስ ድረስም ይገርፉት ዘንድ አዘዘ እርሱም እግዚአብሔርን ፈጽሞ ያመሰግነው ጀመረ። ከወታደሮችም አንዱ አዘነለትና በጆሮው አሾከሾከ እኔ ስለአንተ አዝናለሁ ጉልምስናህንም ላድን እወዳለሁ አንተ ለአማልክትም እንደምትሠዋ ለመኰንኑ አንዲት ቃልን ብቻ ተናገር እኔም እዋስሃለሁ አለው። ቅዱሱም ሰይጣን ከኋላዬ ሒድ ብሎ ገሠጸው። መኰንኑም ጭካኔውን አይቶ ሥጋው እስከ ሚቆራረጥ ደሙም እንደ ውኃ በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ሥቃዩን እጥፍ ድርብ አደረገበት። ከዚህም በኋላ በውኃ እንዲዘፍቁት በእግሩም እንዲጐትቱትና በወህኒ ቤት እንዲጥሉት አዘዘ በዚያም ነፍሱን አሳለፈ ገድሉንም ፈጸመ። የምታምን ሀብታም ሴት መጥታ ለወታደሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥታ የቅዱሱን ሥጋ ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው የወርቅ ሣጥንም አሠርታ በውስጡ አኖረችው። ሥዕሉንም አሣለች በፊቱም ሁልጊዜ የሚያበራ ፋና አኖረች። ለዚችም ሴት ቅዱሱ ያደረገላት የድካም ዋጋዋ ሰኔ አንድ ቀን ተጽፎ አለ።
➯ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
#ስንክሳር ሐምሌ 22 እና #ከገድላት_አንደበት
3July 28, 2026 478