የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ለ9ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 251 የጤና ባለሙያዎች… — Addis Ababa Health Bureau / አዲስ አበባ ጤና ቢሮ / AACAHB / — TG.ME

የካቲት 12  ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ለ9ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 251 የጤና ባለሙያዎች አስመርቋል።
 
አ/አ/ጤ/ቢሮ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም

 
ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጁ ለ9ኛ ዙር  በቅድመ ምርቃ መርሃ-ግብር በዶክትሬት ዲግሪ ፣ በነርሲንግ እና ህክምና ላብራቶሪ እንዲሁም በድህረ ምርቃ በስፔሻሊቲ እና ሰብስፔሊቲ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት 251 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
 
በምርቃት ስነ- ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች ዶክተር ዱሬቲ ጀማል እና ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ፣ የሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አበበ ታደሰ ፣ የኮሌጁ የሴኔት አባላት ፣ የጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት ፣ የሆስፒታል ኮሌጁ ኃላፊዎች እና መምህራን ፣ ተመራቂዎች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል ።

የዕለቱ የክብር እንግዳ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዱሬቲ ጀማል በከተማ አስተዳደሩ ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት በሽታን ከመከላከል በተጨማሪ አክሞ ማዳንን በማካተት እየተተገበረ ላለው የጤና ፖሊሲ አዳዲስ የጤና ተቋማትን በመገንባት እና ነባሮቹን በማስፋት እንዲሁም  ዘመኑን የዋጁ የህክምና ግብዓት በማሟላት ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት በመስጠት  አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የጤና አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የጤና የአገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
 
በመዲናዋ የእናቶችን እና ህጻናትን ጤና ለመጠበቅ  ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እና አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዱሬቲ በተለይም የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም መተግበሩ ለሌሎች የአፍሪካ እና የአለም ሀገራት ተሞክሮ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማስቀጠል የሰለጠነ የሰው ሃይል ወሳኝ በመሆኑ የዛሬ ተመራቂ የህክምና ባለሙያዎች በገባችሁት ቃል መሰረት ህሙማንን ለመርዳት የበኩላቸውን እንዲወጡ እና በተለይም የጤና ሙያ ሁልጊዜ አቅምን ማሳደግ ፣ በርህራሄ እና በቀና ማገልገልን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንን በትጋት እንዲፈጽሙ አሳስበዋል፡፡
 
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አበበ ታደሰ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ኮሌጁ ለ 103 አመታት በጤናው ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዛሬው ዕለትም በተለያዩ የሙያ መስክ የተመረቁት 251 የጤና ተመራቂዎች እያደገ የመጣውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ጠቅሰዋል ።

ሆስፒታል ኮሌጅ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም የህክምና ኮሌጅ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አበበ ታደሰ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ሆኖ ከተቋቋመበት 2004 ዓ.ም ጀምሮ 1ሺህ 223 ብቁ የህክምና ባለሞያዎችን ያፈራና በአጭር ጊዜ ዉስጥ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ  መሆኑን ገልጸው ተቋሙ  በቅድመ ምረቃ  የህክምና ዶክተሬት ትምህረት የጀመረውን  ጉዞ ዛሬ ላይ በርካታ ስፔሻሊቲ እና ሰብ እስፔሻሊቲን ያካተተ 21 ፕሮግራሞችን ከፍቶ በማስተማርና በማስመረቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል  ፡፡
 

በዕለቱ የተመረቁ የመጀመሪያ ዲግሪ  ተመራቂዎች ሙያው የሚጠይቀውን ሁሉ  ለመፈፀም ቃለመሃላ  የፈፀሙ ሲሆን  ከየሙያ ዘርለፉ  የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።
❤8👏3
September 5, 2026 1.7K 1